የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "በእስራኤል እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ያለው ሰላም የጊዜ ጉዳይ ነው" ብለዋል
ሳዑዲ አረቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍልስጤም አምባሳደር መድባለች።
ከእስራኤል ጋር መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመስረት እያሰበ ያለው የሳዑዲ አረቢያ መንግስት፤ ለፍልስጤም አዲስ አማባሳደር መመደቡ ጉዳዩን አነጋጋሪ አድርጎታል።
በአንጻሩ የፍልስጤም ባለስልጣናት የሳዑዲ አረቢያ የመጀመሪያ አምባሳደርን በደስታ መቀበላቸው ተነግሯል።
- አረብ ኢምሬትስ፣ ቻይና እና ፈረንሳይ የተመድ የጸጥታው ም/ቤት በፍልስጤም ጉዳይ ስብሰባ እንዲያደርግ ጠየቁ
- “የአብርሃም ስምምነትን” ተከትሎ እስራኤል እና ፍልስጤም ድርድር እንዲያደርጉ የተመድ ዋና ጸሐፊ አሳሰቡ
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሃሙድ አባስ ዲፕሎማሲያው ጉዳዮች አማካሪ ማይጂድ አል ከሃሊዲ የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር የሹመት ደብዳቤ ቅጂ መቀበላቸውም ታውቋል።
ማይጂድ አል ከሃሊዲ የሳዑዲ አረቢያ ውሳኔ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደፊት የበለጠ ለማጠናከር እንደሁም፣ ጠንካራ ወንድማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ያግዛል ሲሉ አወድሰዋል።
በፍልስጤም የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር ሆነው የተመደቡት አምባሳደር ናይፍ አልሱዳይሪ፤ በዮርዳኖስ የሳዑሲ አምባሳደር ሲሆኑ፤ በእየሩሳሌም ጄነራል ኮንሱሌትን ሸፍነው ይሰራሉ ተብሏል።
የሳውዲ ልዑክ ሹመቱን "አስፈላጊ እርምጃ" ያሉ ሲሆን፤ የንጉስ ሳልማን እና የልዑል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማንን "ከፍልስጤም ግዛት ወንድሞች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና በሁሉም መስኮች መደበኛ የሆነ እድገትን ለመስጠት ያለውን ፍላጎት የሚያጎላ ነው" ብለዋል።
እስራዔል በበኩሏ አዲሱ የሳዑዲ አረቢያ ልዑክ በእየሩሳሌም ውስጥ መቀመጫ ስፍራ አያገኝም ስትል ዝታለች።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊ ኮኸን በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት "በእስራኤል እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ሰላም የጊዜ ጉዳይ ነው" ብለዋል።