የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከእስራኤል አቻቸው ጋር በመነጋራቸው ከስራ ታገዱ
ሊቢያ ከእስራኤል ጋር ንግግር ማድረጓን ተከትሎ በትሪፖሊና ሌሎች ከተሞች አመጽ ተቀስቅሷል
በትሪፖሊ ተቃዋሚዎችም የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ ዲቤባህ በመኖሪያ ቤት ላይ እሳት ለኩሰዋል
የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከእስራኤል አቻቸው ጋር መነጋገራቸው መሰማቱን ተከትሎ በትሪፖሊ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች አመጽ ተቀስቅሷል።
ሊቢያ ለእስራኤል እንደ ሀገር እውቅና የማትሰጥና ፍልስጤምን የምትደግፍ መሆኑን ተከትሎ ነው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከእስራዔል ከፍተኛ ዲፕሎማት ጋር መወያየታቸው ቁጣን የቀሰቀሰው።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ከሊቢያዋ አቻቸው ናጅላ አል ማንጎሽ ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ግንኙነት ለማስጀመር የሚችል የመጀመሪያ ታሪካዊ ንግግር አድርገናል ብለዋል።
እስራኤል ከአረብ ሀገራት እንዲሁም በርካታ የሙስሊም ማህበረሰብ ካላቸው ሀገራት ጋር ግንኙንት ለመፍጠር እየሰራች ሲሆን፤ ለበነዳጅ ሀብት የበለጸገችው ሊቢያም አንዷ ነች።
ሆኖም ግን ሶስት ግዛቶችን የሚወክለው የሊቢያ ፕሬዝዳንታዊ ምክር ቤት ከእስራኤል ጋር ያለውን ግንኙነት መደበኛ ማድረግን ህገ ወጥ ነው በማለት ተቃውሟል።
የሊቢያ ፓርላማ ቃል አቀባይም፤ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናጅላ አል ማንጎሽ የፈጸሙት ተግባር ትልቅ የሆነ የሀገር ክደት ነው ሲሉ ከሰዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ ዲቤብህ ምርመራ እንዲደረግ አዘዋል።
በሞቶዎች የሚቆጠሩ ሊቢያውያንም በትሪፖሊ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ቁጣቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
በማህበራዊ ትስር ላይ የተለቀቁ ምስሎች እንደሚያሳዩት ተቃዋሚዎች በሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ፊት ለፊት ተሰብስበው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናጅላ አል ማንጎሽ ከስልጣን እንዲባረሩ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ተቃዋሚዎች በሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ ዲቤብህን በመኖሪያ ቤት ፊት በመሰብሰብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንዲለቁ የጠየቁ ሲሆን፤ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ እሳት ለኩሰዋል ነው የተባለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ ዲቤብህ በወቁቱ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ስለመኖረራቸው የተረጋገጠ ነገር የለም ተብሏል።