ሳኡዲ ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን እያደሰች ነው - መሀመድ ቢን ሳልማን
ሪያድና ቴል አቪቭ በዋሽንግተን አማካኝነት የሰላም ስምምነት ለመፈራረም የጀመሩት ንግግር አለመቋረጡንም የሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ ተናግረዋል
የፍልስጤማውያን ጥያቄ ምላሽ ያግኝ የሚለው የሳኡዲ ጥያቄ በእስራኤል ምላሽ ያገኛል ወይ የሚለው አጠያያቂ ሆኗል
የሳኡዲ አረቢያ እና እስራኤል ግንኙነታቸውን ለማደስ የጀመሩት እንቅስቃሴ “በየቀኑ ይበልጥ እንዲቀራረቡ” እያደረጋቸው መሆኑን የሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ተናገሩ።
ልኡል አልጋ ወራሹ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሪያድ እና ቴልአቪቭ ግንኙነትን የማደስ ጥረት “በየቀኑ መቀራረብን” እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
“ለእኛ የፍልስጤም ጉዳይ ወሳኝ ነው” ያሉት ሞሀመድ ቢን ሳልማን፥ የፍልስጤማውያን ጥያቄ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት አሳስበዋል።
በአሜሪካ አደራዳሪነት ሳኡዲ እና እስራኤልን ለማቀራረብና የሰላም ስምምነት እንዲፈርሙ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ የፍልስጤም ነጻ ሀገር መሆን በሪያድ በኩል እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል።
ሳኡዲ የፍልስጤምን ጉዳይ መሰረታዊ ነው ብትልም የሰላም ንግግሩ ግን በየቀኑ ለውጥ የሚያሳይ ስለመሆኑ ያነሱት ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን፥ ንግግሩ ተቋርጧል በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሀሰት ነው ብለዋል።
ለመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ኒውዮርክ የሚገኙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ስለሰላም ስምምነቱ መክረዋል ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
የሰላም ስምምነቱ የአረብ- እስራኤል ግጭትን ለማስቆምና እስያ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓን የሚያስተሳስር የኢኮኖሚ ኮሊደር ለመክፈት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ተብሏል።
ሳኡዲ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ስትፈርም ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል የኒዩክሌር ጣቢያን ለመገንባት በአሜሪካ ቃል ተገብቶላታል።
ስለኢራን የኒዩክሌር ፕሮግራም የተጠየቁት ልኡል አልጋወራሹ፥ “ማንኛውም ሀገር የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ መታጠቁ ያሳስበናል፤ ኢራን አንድ የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ ካላት ሳኡዲም አንድ ይኖራታል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሳኡዲ አረቢያ በየመን ከሃውቲ አማጺያን ጋር ስታደርገው የነበረውን ጦርነት አቁማ ተፋላሚዎቹ በሪያድ ድርድር እንዲጀምሩ አድርጋለች፤ ሶሪያም ዳግም ወደ አረብ ሊግ እንድትመለስ ትልቁን ሚና ተጫውታለች።
በመጋቢት ወርም በቻይና አደራዳሪነት ከኢራን ጋር ግንኙነቷን ለማደስ ተስማምታ ሀገራቱ ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተዋል።
ሪያድ ከእስራኤል ጋር እያደረገችው ያለው የሰላም ድርድርም የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ጂኦፖለቲካን እንደሚቀይር ይታመናል።