በሳኡዲ አረቢያ በሞት የሚቀጡ ሰዎች በከፍተኛ ቁጥር መጨመራቸው ተገለጸ
በ2024 330 ሰዎች በሞት የተቀጡ ሲሆን ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ብልጫ ያለው ነው ተብሏል
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የንጉሳዊ አስተዳደሩ ከፍተኛ ያልሆኑ ወንጀለኞችን ጭምር በሞት እየቀጣ ነው ሲሉ ታቀውሞ አቅርበዋል
ሳኡዲ አረቢያ በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የፈረንጆቹ 2024 አመት በሞት የቀጣቻቸው ሰዎች ቁጥር በአስርተ አመታት ውስጥ ከፍተኛው እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ሀገሪቱ በልዑል አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን በተዋወቀው ራዕይ 2030 ማዕቀፍ ጠንካራ ሀይማኖታዊ ገደቦች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመቀነስ ስሟን ወደ ቱሪዝም እና መዝናኛ ማዕከል ለመቀየር ጥረት እያደረገች ቢሆንም ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር ተያይዞ ዛሬም ስሟ መነሳቱ አልቀረም፡፡
በ2024 በሞት የቀጣቻቸው 330 ሰዎች ቁጥር ከባለፈው አመት አንጻር ሲወዳደር በእጥፍ የጨመረ ሲሆን በአስርት አመታት ውስጥ ደግሞ ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡
በተለያዩ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የወጣው እና ሮይተርስ አረጋግጨዋለሁ ባለው መረጃ ሀገሪቱ በ2022- 196 ሰዎች በሞት የቀጣች ሲሆን በ2023 ደግሞ 172 ሰዎች ተቀጥተዋል፡፡
በዚህኛው አመት በተፈጸሙ የሞት ቅጣቶች ውስጥ ከፍተኛ ወንጀል ያልፈጸሙ እና መንግስትን የሚቃወሙ ቁጥራቸው 150 የሚጠጉ ዜጎች ጭምር ሰለባ እንደሆኑ የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ፡፡
100 የሚጠጉ ከአፍሪካ ከእስያ እና ከመካከለኛው ምስራቅ የመጡ የውጭ ሀገራት ዜጎች በተጨማሪ ቅጣቱ ተፈጻሚ የሆነባቸው ናቸው፡፡
ከዚህ ባለፈም ህጻናትን ጨምሮ የሞት ፍርድ የሚወሰንባቸው ሰዎች ከመገደላቸው በፊት የተለያዩ መረጃዎችን እንዲያወጡ ስቃይ እና እንግልት ይደርስባቸዋል ተብሏል፡፡
ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ የሚቀርብበትን ክስ የሚያስተባብለው ንጉሳዊ አስተዳደሩ በበኩሉ የሞት ፍርድ ውሳኔ የሚተላለፍባቸው የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት እደጋ ላይ የጣሉ ፣ እጽ ሲያዘዋውሩ የተገኙ እና ሌሎች ከፍተኛ ወንጀሎችን የፈጸሙ ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ይከራከራል፡፡
ከ2017 ጀምሮ የሳኡዲን አስተዳደር በዋናነት የተቆጣጠሩት ልዑል አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ተቃዋሚዎችን በማሳደድ እና በመግደል በሰብአዊ መብት ጥሰት በተደጋጋሚ ይወቀሳሉ፡፡