ደቡብ ሱዳን ለፓርላማ አባላት ያለደመወዝ የአራት ወራት እረፍት ሰጠች
ሀገሪቱ በሱዳን የተከሰተው ጦርነት ምክንያት ነዳጇን ለዓለም ገበያ ማቅረብ አልቻለችም
ደቡብ ሱዳን በገጠማት የበጀት ቀውስ ምክንያት የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ከተከፈላቸው 10 ወር አልፏቸዋል
ደቡብ ሱዳን ለፓርላማ አባላት ያለደመወዝ የአራት ወራት እረፍት ሰጠች፡፡
ጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የተባለ የገንዘብ ቀውስ የገጠማት ሲሆን ተቋማት ለሰራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል አልቻሉም፡፡
በሱዳን ያጋጠመው የእርስ በርስ ጦርነት የፕሬዝዳንት ሳልቫኪር መንግስት ከፍተኛ የተባለ የበጀት እጥረት እንዲያጋጥመው ዋነኛው ምክንያት ሆኗል፡፡
ኢኮኖሚዋ በነዳጅ ንግድ ላይ የተመሰረተው ደቡብ ሱዳን ነዳጇን በፖርት ሱዳን በኩል ለዓለም ገበያ ስታቀርብ የነበረ ቢሆንም በሀገሪቱ ያጋጠመው የእርስ በርስ ጦርነት ነዳጅ እንዳትልክ አድርጓታል፡፡
ይህን ተከትሎ ሀገሪቱ ላለፉት 10 ወራት የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ያልተከፈላቸው ሲሆን አሁን ደግሞ የህግ አውጪ ምክር ቤት አባላትን ያለደመወዝ የአራት ወር እረፍት ሰጥታለች፡፡
አስቸኳይ ጉዳይ ካጋጠመ የፓርላማ አባላቱ ይጠራሉ የተባለ ሲሆን እስከዚያው የበጀት እጥረቱን ለማስታገስ በሚል የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ ዶቸቪሌ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የ738.2 ሚሊየን ዶላር ብድር ሰጠች
ደቡብ ሱዳን የውጪ ንግዷ በፖርት ሱዳን ላይ ብቻ የተመሰረተ ሲሆን አማራጭ የንግድ መስመሮችን በማፈላለግ ላይ ትገኛለች፡፡
ለአብነትም ነዳጅ እና ሌሎች የውጭ ግብይቶችን በኢትዮጵያ በኩል አድርጋ የጅቡቲ ወደብን እንደ አማራጭ ለመጠቀም በመንቀሳቀስ ላይ መሆኗ ተገልጿል፡፡
በቅርቡ በቤጂንግ በተካሄደው የአፍሪካ-ቻይና መሪዎች ጉባኤ ላይ የተካፈሉት ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ከቻይና ኩባንያዎች ጋር የመሰረተ ልማት ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ለደቡብ ሱዳን በጋምቤላ በኩል ለሚገነባው የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ወጪ የ738 ሚሊዮን ዶላር ብድር መስጠቷ ይታወሳል፡፡