ኢትዮጵያ የሶማሊያ መንግስት በኢትዮጵያ ጦር ላይ ያቀረበው ክስ አሳዝኖኛል አለች
የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ኃይሎች ከአንድ ቀን በፊት በጊዶ ግዛት የምትገኘውን ዶሎ ከተማ አጥቅተዋል ሲል ከሶ ነበር
ኢትዮጵያ ይህን ያለችው በአንካራ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በአዲስ አበባ ከሶማሊያ ልኡካን ጋር እየመከረች ባለችበት ወቅት ነው
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሶማሊያ ዶሎ ከተፈጠረው ክስተት ጋር በተገናኘ የኢትዮጵያን ጦር መክስሱ እንዳሳዘነው ገልጿል።
የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ኃይሎች ከአንድ ቀን በፊት በጊዶ ግዛት የምትገኘውን ዶሎ ከተማ አጥቅተዋል ሲል ከሶ ነበር።
በጥቃቱ የሶማሊያ ጦር፣ ደህንነት እና ፖሊስ ተቋማት ጉዳት እንደደረሰባቸው እንዲሁም በሶማሊያ ጦር አባላት ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ማጋጠሙን ሚኒስቴሩ በመግለጫው ጠቅሷል።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሶማሊያ ያቀረበችው ክስ እውነትነት የለውም ብሏል።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ክስተቱ የተፈጠረው ኢትዮጵያዊ እና ሶማሊያ በወደብ ስምምነት ምክንያት ተበላሽቶ የነበረውን ግንኙነታቸውን ለማደስ የሚያደርጉትን ጥረት ለማወክ በሚሹ አካለት ነው።
ኢትዮጵያ "በሶስተኛ ወገን የሚፈጸም ጥቃት ሁለቱ ሀገራት ለአንካራ ስምምነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ችግር ውስጥ እንዲያስገባው መፈቀድ የለበትም"፤ እንዲህ አይነት ክስተት እንዳይኖር ከሶማሊያ መንግስት ጋር ትሰራለች ብሏል ሚኒስቴሩ።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ አዲስ አመት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር በፈረመችው ስምምነት ምክንያት ነበር ከሶማሊያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ የገባችው። ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ የምታየው ሞቃዲሹ የኢትዮጵያን አምባሳደር በማባረረ ጭምር ቁጣዋን መግለጿ ይታወሳል።
ሀለቱ ሀገራት አለግባባታቸውን ለመፈታት በቱርክ አስተናጋጅነት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በኩል በሁለት ዙር ንግግር ያደረጉ ሲሆን በመሪዎች ደረጃ የተካሄደው ሶስተኛው ዙር ድርድር በስምምነት ተጠናቋል።
የቱርኩ ፕሬዝደንት ታይፕ ኢርዶጋን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የሶማሊያውን ፕሬዝደንት አለመግባባታቸውን ኢንዲተው ከሳምንታት በፊት በአንካራ አስማምተዋቸዋል።
"አንካራ ዲክላሬሽን" ተብሎ በተሰየመው ስምምነት ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉአላዊነት ባከበረ መልኩ ወደብ የመጠቀም መብቷን እንዲከበር ሚያስችል ነው።
ሶማሊያ በኢትዮጵያ ኃይሎች ላይ ክስ ያቀረበችው የአንካራውን ስምምነት ለማጽናት የሉኡክ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መላኳ በተሰማበት ወቅት ነው።
በትናንትናው እለት በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ የተመራ ቡድን ወደ አዲስ አበባ ልካለች።
የሁለቱ ሀገራት ደህንነት ኃፊዎች በዛሬው እለት መምከራቸውን የብሔራዊ ደህንነት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን በኤክስ ገጻቸው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና ሶማሊያ አለመግባባት ምክንያት በቀጠናው አዳዲስ ሁነቶች ተስተውለዋል።
በአባይ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ የምትገኘው ግብጽ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እስከማድረግ ደርሳለች። ግብጽ በአዲሱ የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ተልኮ ውስጥ ወታደር እንደምታዋጣም የመከላከያ ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።
ከስምምነቱ በኋላ በሶማሊያ ውስጥ ለአስርት አመታት የቆየው የኢትዮጵያ ጦር በአዲሱ የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ስለመካቱት ወይም ስለአለመካቱት የታወቀ ነገር የለም።