በሱዳን በአምስት አካባቢዎች ረሃብ መከሰቱን የሚያመላክት ሪፖርት ይፋ ሆነ
24.6 ሚሊየን ሱዳናውያንም አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል
የሱዳን ጦር በተመድ የሚደገፈው የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴ ያወጣውን ሪፖርት ተቃውሟል
በሱዳን በአምስት አካባቢዎች ረሃብ መከሰቱንና እስከ ግንቦት ወር ድረስም በተጨማሪ አምስት አካባቢዎች ሊዛመት እንደሚችል አለማቀፉ የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴ (ኤፍአርሲ) ገለጸ።
ኮሚቴው ትናንት ይፋ ባደረገው ሪፖርት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው አቡ ሹክ እና አል ሳላም ካምፖች፣ ሰሜን ዳርፉር እና ኑባ ተራራዎች ረሃብ መከሰቱን አመላክቷል።
በሰሜን ዳርፉር ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎችን ያስጠለለው ዘምዘም ካምፕ ውስጥ ረሃብ መከሰቱንም ነው የጠቆመው።
በመንግስታቱ ድርጅት የሚደገፈው የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴ በሪፖርቱ በካዳህ፣ ሜሊት፣ አል ፋሺር፣ ታዊሻ እና አል ላይት በተባሉ አምስት አካባቢዎች በግንቦት ወር ረሃብ ሊከሰት እንደሚችልም ትንበያውን አስቀምጧል።
24.6 ሚሊየን ሱዳናውያን (ከሀገሪቱ ህዝብ ግማሹ) አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ይሻል ያለው ሪፖርቱ፥ የረሃብ አደጋ አንዣቦባቸዋል ያላቸውን 17 አካባቢዎችም ይፋ ማድረጉን ሬውተርስ ዘግቧል።
በሱዳን ጦር የሚመራው መንግስት ይህ ሪፖርት ከመውጣቱ በፊት ከኮሚቴው ጋር ትብብሩን ማቋረጡን ማስታወቁ ይታወሳል።
የግብርና ሚኒስትሩ አቡ በከር አል በሽሪ ሪፖርቱ "የሱዳንን ሉአላዊነት የሚጋፋ እና አሳማኝ መረጃዎችን ያልያዘ" በሚል ውድቅ ማድረጋቸውም ተዘግቧል።
አለማቀፉ የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴ (ኤፍአርሲ) በበኩሉ ለሱዳናውያን የከፋ ረሃብ ውስጥ መግባት የሀገሪቱ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑን አስታውቋል።
የሱዳን መንግስት ሀገሪቱ ወደ ከፋ የረሃብ ቀውስ እየገባችም አለማቀፍ ለጋሾች በፍጥነት እንዲደርሱ ወሳኝ የሆነው ሪፖርት እንዳይወጣ እንቅፋት መሆኑንም በማከል።
በሚያዚያ 2023 የተጀመረው የሱዳን ጀነራሎች ጦርነት ከ24 ሺህ በላይ ዜጎችን ህይወት ቀጥፎ ከ14 ሚሊየን በላዩን ከቀያቸው አፈናቅሏል ይላል የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት።
የ20 ወሩ ጦርነት ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት ቻድ፣ ግብጽ እና ደቡብ ሱዳን እንዲሰደዱም አድርጓል።
በተመድ የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ከፍተኛ ባለሙያዋ ዴርቭላ ክሌሪ በሱዳን 638 ሺህ ሰዎች እየተራቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ሱዳን በ15 አመታት ውስጥ ረሃብ እንደተከሰተባት አለማቀፍ ሪፖርት የወጣባት ሶስተኛዋ ሀገር ሆናለች፤ ከሶማሊያና ደቡብ ሱዳን በመቀጠል።
የአለማቀፉ የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴ በሱዳን ረሃብ በ5 አካባቢዎች ረሃብ ተከስቷል በሚል ያወጣው ሪፖርት በአብዱልፈታል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫናውን ያበረታዋል ተብሏል።