ፊፋ የሳኡዲን የ2034 የአለም ዋንጫ አዘጋጅነት በይፋ አጸደቀ
የአለም ዋንጫን 100ኛ አመት በማስመልከት በ2030ው የአለም ዋንጫ ሶስት ጨዋታዎች በኡራጓይ፣ ፓራጓይ እና አርጀንቲና እንዲደረጉም ተወስኗል
ሪያድ የአለም ዋንጫውን ለማዘጋጀት ከሚያስፈልጓት 15 ስታዲየሞች የአራቱን ግንባታ በማካሄድ ላይ ናት
የአለማቀፉ የእግርኳስ ማህበር (ፊፋ) ሳኡዲ አረቢያ የ2034ቱን የአለም ዋንጫ ለማስተናገድ በብቸኝነት ያቀረበችውን ጥያቄ በይፋ ተቀበለ።
211 የፊፋ አባል ፌደሬሽኖች ትናንት ፕሬዝዳንቱ ጂያኒ እንፋንቲኖ በመሩት የቪዲዮ ስብስባ ላይ ተሳትፈዋል።
በዚህም ሳኡዲ ከአስር አመት በኋላ የሚካሄደውን የወንዶች የአለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ ከ200 በላይ ተወካዮች ድምጽ እንደሰጧት ነው የተገለጸው።
ስፔን፣ ፖርቹጋል እና ሞሮኮ ደግሞ የ2030ውን የአለም ዋንጫ እንደሚያዘጋጁ በይፋ ተገልጿል።
የአለም ዋንጫ በ2030 100ኛ አመቱን ስለሚይዝም የውድድሩ ቀዳሚ አስናታጋጅ በሆነችው ኡራጓይ፣ በፓራጓይ እና አርጀንቲና ሶስት ጨዋታዎች እንዲካሄዱ መወሰኑን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የትናንቱ የፊፋ ጉባኤ የተካሄደው በበይነ መረብ እንደመሆኑ መራጮች እጃቸውን እያወጡ ድምጽ አልሰጡም። ይልቁንም ከካሜራቸው ፊት ለፊት በማጨብጨብ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
ከቪዲዮው ድምጽ አሰጣጥ በፊትም ሁሉም ፌደሬሽኖች አስቀድመው ድምጻቸውን መስጠታቸውን የፊፋ ዋና ጸሃፊ ማቲያስ ግራፍስትሮም ተናግረዋል።
የእንግሊዝ እግርኳስ ፌደሬሽን ደጋፊዎቹ በሳኡዲ ደህንነታቸው እንደሚጠበቅ ማረጋገጫ በማግኘቱ ለሪያድ የ2034 የአለም ዋንጫ አዘጋጅነት ጥያቄ ድጋፉን መስጠቱን አስታውቋል።
ኖርዌይ የፊፋ የአለም ዋንጫ አዘጋጅነት ፉክክር ላይ ቅሬታ አለኝ በሚል ድምጽ ከመስጠት ተቆጥባለች።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተሟጋቾች ፊፋ ሳኡዲን የአለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ መፍቀዱን ተቃውመዋል።
የሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ባወጡት መግለጫ "ልዩ የአለም ዋንጫ ለማዘጋጀትና ከመላው አለም ወደ ሀገራችን የሚመጡ የእግርኳስ አፍቃሪዎች ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን" በሚል የፊፋን ውሳኔ አድንቀዋል።
የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ እንፋንቲኖ በበኩላቸው የ2034ቱ የአለም ዋንጫ ሪያድ የሴቶችን መብትና ነጻነት ለማክበር የጀመረችውን ጥረት ለማፋጠን እንደሚያግዛት ይታመናል ብለዋል።
መሰል የሰብአዊ መብት ክሶችና ወቀሳዎች ኳታር የ2022ቱን የአለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ ሲፈቀድላትም ሲነሱ እንደነበር ይታወሳል። ዶሃ በልዩ ዝግጅት ደማቅ የአለም ዋንጫን በማዘጋጀት ስጋቱ ከንቱ እንደነበር አሳይታለች።
ሳኡዲ አረቢያ የ2034ቱን የአለም ዋንጫ ለማዘጋጀት በብቸኝነት ጥያቄውን ካቀረበች በኋላ ዝግጅቷን ጀምራለች።
ለውድድሩ ከሚያስፈልጋት 15 ስታዲየሞች ውስጥ የአራቱን ግንባታ እያካሄደች ትገኛለች።