የ2034 የአለም ዋንጫ አዘጋጅ ሳኡዲአረብያ በስታድየሞች ውስጥ የአልኮል መጠጥ ልትከለክል ነው
በሳኡዲ የአልኮል መጠጥ መሸጥ ክልክል ሲሆን በሀገሪቱ ለዲፕሎማቶች ብቻ የተፈቀደ አንድ የመጠጥ መሸጫ ሱቅ ይገኛል
በኳታሩ የአለም ዋንጫ ፊፋ ለመጠጥ አምራች ስፖንሰሮቹ 40 ሚሊየን ፓውንድ የኪሳራ ማካካሻ ክፍያ መክፈሉ ይታወሳል
የ2034ቱን የአለም ዋንጫ የምታዘጋጀው ሳኡዲ አረብያ በስታድየሞች ውስጥ የአልኮል መጠጥ እንዳይሸጥ ልትከለክል መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ማንም ሀገር ለማዘጋጀት ጥያቄ ባላቀረበበት የ2034 የአለም ዋንጫ ውድድሩን ለማዘጋጀት ብቸኛ ጥያቄ አቅራቢ የነበረችው ሪያድ ዋንጫውን እንድታዘጋጅ በቅርቡ ይፋዊ ፈቃድ ማግኝቷ ይታወሳል፡፡
የአለም አቀፍ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ማህበር ፊፋ በጉዳዩ ላይ ይፋዊ ምላሽ ባይሰጠም ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ከከፍተኛ አመራሮች አገኝሁት ባለው መረጃ መሰረት ማህበሩ የሀገሪቱን ውሳኔ ለማስቀየር ጫና እንደማያዳርግ ዘግቧል፡፡
የ2022 የአለም ዋንጫ አዘጋጅ የነበረችው ሌላኛዋ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገር ኳታር በተመሳሳይ የአልኮል ሽያጭን በስታድየሞች መሸጥ መከልከሏን ተከትሎ ከማህበሩ በተደረገባት ጫና ውድድሩ ሊካሄድ ሁለት ቀናት ሲቀሩት ከአዘጋጅነት ራሷን እንደምታገል አስታውቃ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በወቅቱ የማህበሩ አመራሮች በዶሃ ላይ ሲያደርጉት የነበረውን ጫና በመተው የሀገሪቱን ውሳኔ በመቀበል በሌሎች ሀገሮች እንደሚደረገው በስታድየሞች ውስጥ መጠጥ ሳይሸጥ ውድድር ተካሂዷል፡፡
በዚህም ምክንያት ፊፋ ይፋዊ ስፖንሰር የሆነው የአሜሪካ የቢራ አምራች ኩባንያ “በድዋይዘር” በስታድየሞች አካባቢ አስቀምጧቸው የነበሩ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የቢራ በርሚሎችን እንዲያስወግድ አድርጓል፡፡
በዚህም ፊፋ ኩባንያው ለደረሰበት ኪሳራ ማካካሻ 40 ሚሊየን ፓውንድ ለመክፈል ተገዷል፡፡
ከ1986 ጀምሮ የፊፋ ይፋዊ የማስታወቂያ ስፖንሰር አጋር ሆኖ የዘለቀው “በድዋይዘር” እስከ 2026 ድረስ ከማህበሩ ጋር ኮንትራት ያለው ሲሆን በሚቀጥለው አመት የሚዘጋጀውን የአለም ክለቦች ዋንጫንም ስፖንሰር የሚያደርግ ይሆናል፡፡
በኳታሩ የአለም ዋንጫ በስታድየሞች አካባቢ ቢራ መሸጥ ቢከለከልም በሬስቶራንቶች እና ሆቴሎች ውስጥ ደጋፊዎች የአልኮል መጠጥ የሚያገኙበት አጋጣሚ ነበር፡፡
ከኳታር የበለጠ “ወግ አጥባቂ” በሆነችው ሳኡዲ አረብያ ግን ይህ በቀላሉ የሚሳካ አይመስልም ሲል ዘ ጋርዲያን አስነብቧል፡፡
በእስልምና ህግ የሚመራው የሳኡዲ ንጉሳዊ አስተዳደር በንጉስ ኢብን ሳኡድ ጊዜ ከ1952 ጀምሮ በሀገሪቱ የአልኮል መጠጥ እንዳይሸጥ መከልከሉ ይታወሳል፡፡
በሀገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ዲፕሎማቶች በተወሰነ መጠን ምርቶችን የሚያቀርብ አንድ የመጠጥ መሸጫ ሱቅ ብቻ ይገኛል፡፡