“ለአዳዲስ የሰው ልጅ ስልጣኔዎች በር እንድንከፍት እንሻለን”- ልዑል አልጋወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን
የሳዑዲ አረቢያው ልዑል አልጋወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን ሃገራቸው በቀጣዮቹ 10 ዓመታት 3 ትሪሊዬን ሪያል ኢንቨስት ለማድረግ መወጠኗን አስታወቁ፡፡
ልዑል አልጋወራሹ የሃገሪቱን የቀጣይ 5 ዓመታት የልማት ዕቅድ ይፋ ባደረጉበት በትናንትናው ዕለት ነው ይህን ያስታወቁት፡፡
ሳዑዲ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀ ምጣኔ ሃብትን ለመገንባት አቅዳ በመንቀሳቀስ ላይ ነች፡፡ ለዚህ የሚሆኑ እና አዳዲስ የንግድ እና ስራ ፈጠራ እንዲሁም የግሉን ዘርፍ የሚያበረታቱ የልማት ስልቶችን ቀይሳለች፡፡
ይህንኑ ውጥን በመደገፍ ከግብ ለማድረስም የሳዑዲ የኢንቨስትመንት ፈንድ ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
ፈንዱ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ማለትም እ.ኤ.አ እስከ 2030 ከ7 ትሪሊዬን 500 ቢሊዬን ሪያል የሚልቅ ሃብትን እንደሚያካብትም ይጠበቃል፡፡
በየዓመቱ 150 ቢሊዬን ሪያል (40 ቢሊዬን ዶላር) ከዚሁ ሃብት እየተጨለፈ ወደ ሃገሪቱ ምጣኔ ሃብት ፈሰስ እንደሚደረግም ነው ልዑል አልጋወራሹ ዕቅዱን ባስተዋወቁበት ወቅት የተናገሩት፡፡
ይህም በ2025 1 ነጥብ 8 ሚሊዬን የስራ እድልን ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡
መሃመድ ቢን ሰልማን ስለ ዘርፈ ብዙው የልማት ዕቅድ ሲናገሩ ሃገራችን ለአዳዲስ የሰው ልጅ ስልጣኔዎች በር ከፋች እንድትሆን እንሻለን ብለዋል፡፡
ለዚህም አዳዲስ የልማት ዘርፎች እና የግል ባለሃብቱን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ተግባራት እንደሚከወኑም ገልጸዋል፡፡
የሳዑዲ የኢንቨስትመንት ፈንድ በ1971 ነው የተቋቋመው፡፡
የሃገሪቱ የ2030 እቅድ ከ5 ዓመታት በፊት ይፋ ከተደረገ በኋላ ፈንዱ ሊጫወት የሚችለው ሚና እና አጠቃላይ በጀቱም አድጓል፡፡
እስከ 2 ትሪሊዬን ዶላር ሃብት አካብቶ የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት የመምራት የመደገፍ እና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቱን ወደላቀ ምዕራፍ የማሸጋገር እንዲሁም ምጣኔ ሃብቱን ከነዳጅ ጥገኝነት የማላቀቅ ትልቅ ተስፋም ተጥሎበት ነው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው፡፡
እስካሁንም በአምራች፣ በመሰረተ ልማት፣ በባንክ እና በሌሎችም ዘርፎች ላይ መልከ ብዙ እቅስቃሴዎችን አድርጓል፡፡