ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ለመውጣት የሚጠየቁት የቪዛ መቀጫ ተነሳ
በነፍስ ወከፍ ይጠየቅ የነበረው የመውጫ ቪዛ መቀጫው እንዲነሳ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል
መቀጮውን ለማስቀረት የተደረሰው ስምምነት በመጪዎቹ ስድስት ወራት ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል
ሳዑዲ አረቢያ የመውጫ ቪዛ ውዝፍ መቀጮ ክፍያን አነሳች
በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙና ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሳያሳድሱ የቆዩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ በቤተሰብ አባላት ቁጥር በነፍስ ወከፍ ይጠየቁ የነበረውና የመውጫ ቪዛ ውዝፍ መቀጮ ክፍያ እንዲነሳ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ከስምምነት ተደረሰ።
ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሳያሳድሱ በሳዑዲ ዓረቢያ በቆዩ የሁሉም የውጭ አገር ዜጎች ላይ እየተተገበረ የሚገኘውና የመውጫ ቪዛ ለማግኘት በቤተሰብ አባላት ቁጥር በነፍስ ወከፍ በየወሩ ይጠይቅ የነበረው 400 የሳዑዲ ሪያል ውዝፍ መቀጮ ክፍያ በመብዛቱ ምክንያት በርካታ ዜጎች ከዕድሉ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
ስምምነቱ ከሳዑዲ ዓረቢያ ሮያል ኮርት በተሰጠ ምህረትና መመሪያ በልዩ ሁኔታ የተፈቀደ ሲሆን በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን በሳዑዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል፡፡
ኤምባሲውም ይህ ክፍያ እንዲቀንስ ወይም እንዲነሳ ባቀረበው ጥያቄ ላይ ከሳዑዲ ዓረቢያ የመንግስት አካላት ጋር በተደረገ ውይይትና ግፊት የውዝፍ ክፍያው ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ መስማማታቸውን አሳውቋል፡፡
ይህንኑ የአጭር ጊዜ ዕድል ለዜጎች ለማዳረስ እንዲቻል ከሪያድ የኢፌዴሪ ኤምባሲና ጅዳ ቆንስላ ጽ/ቤት በተጨማሪ በመዲና፣ አብሃ፣ ጂዛን፣ ጣኢፍ ከተሞች ጭምር የጊዜያዊ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎቸ ተከፍተው ሂደቱን ለማስጀመር ከሚለከታቸው የሃገሪቱ መንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው ኤምባሲው ያስታወቀው፡፡