መዓዛ ያላቸው ሻማዎች ከሲጋራ ጭስ በበለጠ ለጤና አደጋኛ መሆናቸውን ጥናት አረጋገጠ
ሻማዎቹ በሚለኮሱበት ወቅት የሚለቁት ጭስ ለሳንባ ፣ ለልብ ፣ ካንሰር እና ለሌሎች ተያያዥ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ተነግሯል

አንዳንድ ሻማዎች ከተሸከርካሪ ሞተሮች እና ከሚቃጠል እንጨት ከሚወጡ በካይ ብናኞች እኩል አደገኛ ናቸው ተብሏል
በበዓት እና ልዩ ፕሮግራሞች ላይ የሚለኮሱ መልካም ጠረን ያላቸው ሻማዎች ለመተንፈሻ አካላት በሽታዎች የማጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አዲስ ጥናት አረጋግጧል፡፡
ጥናቱ መዓዛ ያላቸው ሻማዎች የቤት ውስጥ ጠረንን በመቀየር ጥሩ ስሜትን ለመፈጥር ቢያገለግሉም፤ ነገር ግን ሻማዎቹ ሲቀጣጠሉ የሚለቋቸው ኬሚካሎች የሲጋራ ጭስ ከመተንፈስ በበለጠ ጉዳት አላቸው ነው የተባለው፡፡
ሻማዎች ሲቃጠሉ እንደ ካርቦን ሞኖክሳይድ፣ ሰልፈር ዳይኦክሳይድ ፣ ናይትሮጅን ኦክሳይዶችን ጨምሮ መርዛማ ጋዞችን እና ውስብስብ የኬሚካል ብናኞችን ወደ ከባቢ እንደሚለቁ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
እነዚህን ጋዞች በአንድ ላይ ወደ ውስጥ መተንፈስ ሳል፣ ማስነጠስ እና የአይን እብጠትን እንዲሁም የአስም ምልክቶችን ሊያባብስ ይችላል።
በረጅም ጊዜ ሂደት ውስጥ ሻማዎች የሚፈጥሩት የቤት ውስጥ የአየር ብክለት ለልብ ህመም፣ ለሳንባ ካንሰር እና የሌሎች ተያያዝ በሽታዎች ተጋላጭነትን ሊጨምር እንደሚችል ነው የተገለጸው፡፡
ተመራማሪዎች ሻማዎቹን በተለያዩ መኖርያ ቤቶች ውስጥ በተለያየ ሰአት በመለኮስ የጉዳት እና የብክለት መጠናቸውን ለማወቅ ምርምሮችን አድርገዋል፡፡
በዚህም በተደጋጋሚ ለአንድ ሰአት እና ከዛ በላይ መዓዛ ያላቸው ሻማዎች በሚለኮሱባቸው ቤቶች ውስጥ ከተሸከርካሪ ሞተሮች እና ከተቃጠለ እንጨት ሊለቀቁ ከሚችሉ በሰው ዓይን ውስጥ የማይታዩ ቅንጣቶች እኩል በካይነት ያለው ብናኝ ከሻማዎቹ እንደሚለቀቅ አረጋግጠዋል፡፡
ብናኞቹ በምንተነፍሰው አየር አማካኝነት በደም ውስጥ በመቀላቀል ወደ ሳንባ ውስጥ ዘልቀው ሊገቡ እንደሚችሉ ነው ያመላከቱት፡፡
በትናንሽ መጸዳጃ ቤቶች ወይም መኝታ ቤቶች ውስጥ ጥሩ መዓዛ ያላቸው ሻማዎችን መለኮስ የበካይ ንጥረ ነገሮችን መጠን ከፍተኛ እንደሚያደርገውም ተገልጿል፡፡
ሰዎች በበዓላት እና በልዩ ፕሮግራሞች አልያም መጥፎ የቤት ውስጥ ጠረንን ለማስወገድ መዓዛ ያላቸው ሻማዎችን መለኮስ አስፈላጊ ነው ብለው ካሰቡ በቤት ውስጥ በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር መስኮቶችን መክፈት እና ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ላይ እንዲያተኩሩ ተመራማሪዎቹ መምከራቸውን ኔቸር ጆርናል ላይ የወጣው የጥናት ውጤት መክሯል፡፡