“በዩክሬን ጦርነት ለማሸነፍ ሩሲያ ማንኛውንም አማራጭ ልትከተል ትችላለች”- ሰርጌ ላቭሮቭ
በቅርቡ ሩሲያ “ኦሬሽኒክ” ሀይፐር ሶኒክ ሚሳይልን ወደ ዩክሬን ያስወነጭፈችው ይህን መልእክት ለምዕራባውን ለማስተላለፍ ነው ተብሏል

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የኔቶ ወደ ሩስያ ድንበር መጠጋት የሚፈጥረውን ስጋት ለአመታት ስናስጠነቅቅ ቆይተናል ብለዋል
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ማንኛውንም አማራጭ ልትጠቀም እንደምትችል ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአየር መቃወሚያዎች ሊመታ አይችልም ሲሉ የገለጹትን “የኦሬሽኒክ” ሃይፐርሶኒክ ሚሳይል ባለፈው ወር ሞስኮ በዩክሬን ዲኒፕሮ ከተማ ላይ አስወንጭፋለች፡፡
አስፈላጊ ከሆነ ሩሲያ ሌሎች እንደዚህ ያሉ ሚሳይሎችን በጦርነቱ ጥቅም ላይ ልታውል እንደምትችል ላቭሮቭ አስጠንቅቀዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካዊው ጋዜጠኛ ታከር ካርልሰን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልለስ "ይህን መሳርያ በመጠቀም ለማስተላለፍ የፈለግነው መልዕክት አሜሪካ እና አጋሮች የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን ለኪየቭ ሲያቀርቡ ሞስኮ በጦርነቱ ላለመሸነፍ ማንኛውንም ዘዴ ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን ለማስገንዘብ ነው” ብለዋል፡፡
ምዕራባውያን እየተፋለሙ ያሉት በዓለም ላይ በየትኛውም ሀገር፣ በማንኛውም ቀጠና እና አህጉር የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ ነው ያሉት ላቭሮቭ፤ ሀገራቸው እየታገለች የምትገኝው ህጋዊ የደህንነት ጥቅሟን ለማስጠበቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ሩሲያ “ልዩ ዘመቻ” ብላ የምትጠራው የዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ባሉት ወራት እና ሳምንታት በሞስኮ የጸጥታ እና ደህንነት ዋስትና ዙርያ ለመምከር ፍቃደኛ እንዳልነበሩ ነው ያስታወቁት፡፡
“ዩክሬን የግዛት አንድነቷን ለማስጠበቅ እና ጦርነቱ እንዳይጀመር ሁለት ጊዜ የቀረቡላትን የድርድር ሀሳቦች ውድቅ አድርጋለች፤ ይህን ጦርነት እና አልጀመርነውም። የኔቶ ወደ ድንበራችን መጠጋት የሚፈጥረውን የደህንነት ስጋት ለአመታት ስናሳስብ እና ስናስጠነቅቅ ቆይተናል፤ ነገር ግን ሰሚ አልነበርም” ብለዋል፡፡
ለ80 ደቂቃ በቆየው ቃለ ምልልስ ላቭሮቭ ምዕራባውያን ሞስኮ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የማትሻገረው ቀይ መስመር እንደሌለ ሊገነዘቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ላቭሮቭ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮለዲሚር ዘለንስኪ በ2022 መገባደጃ ላይ ያቀረቡትን የሰላም እቅድ እና በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ ይፋ ያደረጉትን “የድል እቅድ” “ከንቱ” ሲሉ አጣጥለውታል።
ከተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን የማስቆም እቅድ ጋር ተያይዞ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩሲያ የብሔራዊ ጥቅሟን እና የደህንነት ጥያቄዋን ያከበረ ማንኛውንም የሰላም ድርድር ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኗን ተናግረዋል፡፡