በጃፓን የመቀስ መጥፋት በርካታ በረራዎች እንዲሰረዙ አደረገ
በፍተሻ ጣቢያ አቅራቢያ ከሚገኝ ሱቅ የጠፉት ሁለት መቀሶች 36 በረራዎች እንዲሰረዙና 201 በረራዎች እንዲዘገዩ ምክንያት ሆነዋል
የጃፓኑ አየርመንገድ የወሰደው እርምጃ ለመንገደኞች ደህንነት ቅድሚያ የሰጠ ነው በሚል ተወድሷል
በጃፓን ሆካይዶ ደሴቶች ውስጥ የሚገኘው የኒው ቺቶስ አውሮፕላን ማረፊያ ባለፈው ቅዳሜ ያልተለመደ ክስተት አጋጥሞታል።
በአውሮፕላን ማረፊያው የፍተሻ ጣቢያ አካባቢ ከሚገኝ ሱቅ ሁለት መቀሶች ጠፍተዋል።
የጠፉትን መቀሶች ፍለጋው ስአታትን መውሰዱም 36 በረራዎች እንዲሰረዙና 201 በረራዎች እንዲራዘሙ ማስገደዱን ነው ቢቢሲ የዘገበው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች በድጋሚ ተፈትሸው ከሁለት ስአታት በኋላ በረራ መጀመሩ ተገልጿል።
የአውሮፕላን ማረፊያው አስተዳዳሪዎች የጠፉት መቀሶች መገኘታቸውን እሁድ እለት ይፋ አድርገዋል።
የጠፉትን መቀሶች ከተገኙት ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጊዜ መውሰዱንም አብራርተዋል።
የኒው ቺቶስ ኤርፖርትን የሚያስተዳድረው ሆካይዶ ኤርፖርት በረራ ያስተጓጎሉት መቀሶች ጠፉበት በተባለው ሱቅ ባለሙያ መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በመቀስ ምክንያት በተራዘሙና በተሰረዙ በረራዎች ምክንያት በርካቶች መንገላታታቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ መቀሶቹ ለሽብር ተግባር ውለው ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ተገንዝቦ አውሮፕላን ማረፊያው የወሰደው እርምጃ ለመንገደኞቹ ደህንነት ቅድሚያ መስጠቱን ያሳያል ያሉ አወድሰውታል።
የጃፓን የትራንስፖርትና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሆካይዶ ኤርፖርት የተፈጠረውን ክስተት መንስኤ በፍጥነት እንዲመረምርና በድጋሚ እንዳይከሰት አሳስቧል።
“ክስተቱ ከጠለፋ ወይም ሽብር ጋር ሊያያዝ እንደሚችል እናውቃለን” ያለው የአውሮፕላን ማረፊያው አስተዳዳሪ፥ ከመጋዘን ጥበት እና የአስተዳደር ክፍተት ጋር በተያያዘ ችግሩ ማጋጠሙን ጠቁሟል።
የኒው ቺቶሴ አውሮፕላን ማረፊያ በርካታ በረራዎችን ከሚያስተናግዱ አውሮፕላን ማረፊያዎች ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍ ነው።
አውሮፕላን ማረፊያው በአለማችን በሀገር ውስጥ በረራ በርካታ መንገደኞችን በማስተናገድ ከአለም ሁለተኛው የሆነው የቶኪዮ ሳፖሮ የአየር መስመር አካል መሆኑንም ኦኤጂ የተባለው የአቪየሽን ጉዳዮች ተንታኝ ኩባንያ ገልጿል።
በ2022 ከ15 ሚሊየን በላይ መንገደኞች የኒው ቺቶሴን አውሮፕላን ማረፊያን መጠቀማቸው ተገልጿል።