በኡጋንዳ መስዋዕት ሳይደረጉ አይቀርም የተባሉ 24 ሰዎች የራስ ቅሎች ተገኙ
የሀገሪቱ ፖሊስ ራሱን “ፈዋሽ ነኝ” ብሎ የሚጠራውንና ሰዎችን ለመስዋዕትነት ሳያቀርብ እንዳልቀረ የተገመተውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውሏል
የራስ ቅሎቹ በተገኙበት መስዋዕት ማቅረቢያ ስፍራ ተጨማሪ የሰዎች ቅሪት አካል ፍለጋ እየተካሄደ ነው
በኡጋንዳ ሰዎችን እንደሚፈውስ የሚናገር ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ዳሙሊራ ጎድፍሬይ የተባለው ግለሰብ ከ24 የሰው ልጅ የራስ ቅሎች ጋር ነው የተያዘው።
የራስ ቅሎቹ መለኮታዊ ሃይል አለኝ የሚለው ጎድፍሬይ መስዋዕት አድርጎ ያቀረባቸው ሰዎች ጭንቅላቶች እንደሆኑ ተገምቷል።
ግለሰቡ የሰው ልጆችን ለመስዋዕትነት ማቅረብን በሚከለክለው ህግ ተከሶ እስከ እድሜ ልክ እስራት ቅጣት ሊተላለፍበት እንደሚችል የኡጋንዳ ፖሊስ ቃል አቀባይ ፓትሪክ ኦንያንጎ ተናግረዋል።
በ”ፈዋሽ ነኝ” ባዩ ጎድፍሬይ የመስዋዕት ማቅረቢያ ስፍራ ከሰዎች የራስ ቅል ባሻገር የእንስሳት ቅሪትና ቆዳ መገኘቱን ቃል አቀባዩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በመዲናዋ ካምፓላ አቅራቢያ በተገኘው የመስዋዕት ማቅረቢያ ስፍራ ተጨማሪ የሰዎች ቅሪት አካል ፍለጋ እየተካሄደ ነው ተብሏል።
ጎድፍሬይ ባህላዊ ሀኪምና መድሃኒት ቀማሚ መሆኑን ይገልጻል።
የኡጋንዳ የባህል ሀኪሞች ማህበር ግን ግለሰቡን እንደማያውቀው በመጥቀስ ልጠየቅበት አልችልም ብሏል።
በኡጋንዳ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ መሰል አስደንጋጭ ነገሮች ተከስተዋል።
ባለፈው ወር ከካምፓላ በ41 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ምፒጂ ከተማ አቅራቢያ የ17 ሰዎች የራስ ቅል መገኘቱን ዘገባው አስታውሷል።
ይህ ግኝትም ሆነ በካምፓላ የተገኘው የ24 ሰዎች የራስ ቅል ባህላዊ እምነት አራማጆቹና “ፈዋሽ ነን” ባዮቹ ግለሰቦች ሰዎችን መስዋዕት እንደሚያደርጉ አመላካች መሆኑ ተገምቷል።
በአፍሪካ ሰዎችን ለመስዋዕትነት ማቅረብ ሃብት እና መልካም እድል እንደሚያመጣና ጠላትን ችግር ላይ ለመጣል እንደሚረዳ የሚያምኑ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እንዳሉ ይነገራል።