ኡጋንዳ የመንግስት ሰራተኞቿ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አዘዘች
ውሳኔው በጤና እክል ምክንያት የሚከሰት የስራ ጫናን ለመቀነስ የተላለፈ ነው
የኡጋንዳ የመንግስት ሰራተኞች በሳምንት ለ2 ሰዓት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል
ኡጋንዳ በሀገሪቱ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ትእዛዝ አስተላለፈች።
የኡጋንዳ የመንግስት ባስተላለፈው ትእዛዝ መሰረትም የሀገሪቱ የመንግስት ሰራተኞች በሳምንት ለ2 ሰዓት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።
የኡጋንዳ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በደብዳቤ ባስተላለፈው መልእክት ነው ሰራተኞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ያዘዘው ተብሏል።
የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ሉሲ ናክዮቤ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያም፤ “ትእዛኡ የተላለፈው የመንግስት ሰራተኞችን ሞት ለመቀነስ እና በህመም ምክንያት የሚፈጠሩ የስራ ጫናዎችን ለማቃለል ነው” ብለዋል።
የኡጋንዳ መንግስት በኤክስ ወይም በቀድሞ ትዊተር ገጽ ባስተላለፈው መልእክትም፤ አዲሱ የመንግስት ሰራተኞች የአካል ብቃት እንቅሳቃሴ ንቅናቄ በአኗኗር ዘይቤ ሳቢያ የሚከሰቱ በሽታዎችንና ጫናዎችን ለማስቀረት ያለመ ነው ብሏል።
ኡጋንዳ ትእዛዙን ያስተላለፈችው በሀገሪቱ ያለው ከልክ ያለፈ ውፍረት መጠን ከ17 በመቶ ወደ 26 በመቶ ክፍ ማከለቱ በጥናት ከተረጋገጠ ከሁለት ዓመት በኋላ ነው።
ኡጋንዳ ዜጎቿ የአካል ብቃት እንዲያድርጉ ስታነሳሳ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም የተባለ ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2018 ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሄራዊ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቀን ሰይማ እንደነበረ ይታወሳል።
በኡጋዳ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ቻርልስ ኦዮ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ፤ የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ሰራተኞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በቋሚነት መስራት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
ይህ በጤና ሚኒስቴር ሰራተኞች የተጀመረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመላው ሀገሪቱ ተስፋፍቶ መመልከት እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።