የ63 ዓመቱ የጋና ባህላዊ የኃይማኖት መሪ የ12 ዓመት ሴት ልጅ ማግባታቸው ቁጣን ቀሰቀሰ
መንግስት ጋብቻውን እንዲያስቆምና ባህላዊ የኃይማኖት መሪው ላይ ምርመራ እንዲደረግ ተጠይቋል
ትችት የተሰነዘረባቸው የማህበረሰብ መሪዎች ህዝቡ በጋብቻው ማውገዙ "ከድንቁርና የመጣ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል
በጋና አንድ ታዋቂ የ63 ዓመት የባህላዊ ኃይማኖት መሪ የ12 ዓመት ታዳጊ ሴት ልጅ ማግባታቸውን ተከትሎ ቁጣን ቀሰቀሰ።
የባህላዊ የኃይማኖት መሪው ቄስ ኑሞ ቦርኬቲ ትሱሩ 33ኛ ቅዳሜ እለት በተካሄደ ባህላዊ ስነ ስርዓት ነው የ12 ዓመት ታዳጊ ሴት ልጅ አገብተዋል።
ደማቁን ባህላዊ የጋብቻ ስነ ስርዓት የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶግራች በማህበራዊ ትስስር ገጾቸ ላይ በስፋት የተሰራጩ ሲሆን፤ በሰርግ ስነ ስርዓቱ ላይም በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መታደማቸው ተነግሯል።
በተለቀቀው ቪዲዮ ላይም አንዲት ሴት “ጋአ” በተባለው የአካባው ቋንቋ ሙሽሪትን ባሏን የሚያማልል ልብስ መልበስ እንዳለባት ስትመክር ታይቷል።
እንዲሁም የ12 ዓመቷን ሙሽሪት ለሚስትነት ተግባር እንድትዘጋጅ እና የሰጧትን ሽቶ በመቀባባት የበሏ የፆታዊ ግንኙነት ፍላጎት እንድታነሳሳ ሲመክሯትም ይደመጣል።
በቪዲዮው ላይ የተሰሙ ንግግሮችም የሰርግ ስነ ስርዓቱ ለደንቡ ብቻ ያለተዘጋጀ እና ከዚያም አልፎ ለጋብቻ መሆኑን ማመላከታቸውን ተከትሎም ቁጣን ቀስቅሷል።
ቁጣቸውን ያሰሙት ሰዎች መንግስት ጋብቻውን ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆምና ባህላዊ የኃይማኖት መሪው ላይ ምርመራ እንዲደረግ ተጠይቋል
ትችት የተሰነዘረባቸው የማህበረሰብ መሪዎች “ቁጣው የመጣው ሰዎች ባህላቸውንና ወጋቸውን ስለማያውቁ ነው” ብለዋል።
ልጅቷ እና ቄሱ አባል የሆኑባቸው የኑንጉዋ ተወላጆች ማህበረሰብ መሪዎች ህዝቡ በጋብቻው ማውገዙ "ከድንቁርና የመጣ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።
በጋና አንድ ሰው ጋብቻ እንዲመሰርት የተቀመጠው ዝቅተኛ እድሜ 18 ዓመት ነው፤ አሁን ላይ በጋና ያለ እድሜ ጋብቻ እየቀነሰ ቢመጣም አልፎ አልፎ ግን መከሰቱ እንደቀጠለ ነው።
“ገርልስ ኖት ብራይድስ” የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ባወጣው መረጃ መሰረት በጋና ውስጥ 19 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች እድሜያቸው 18 ዓመት ሳይሞላ እንደሚያገቡ እና 5 በመቶ ሴቶች ደግሞ 15 ዓመት ሳይሞላቸው ትዳር እንደሚይዙ ያመላክታል።