ፖለቲካ
ኡጋንዳዊው ቲክቶከር የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት መሳደቡን ተከትሎ ለእስር ተዳረገ
የኡጋንዳ ፍርድ ቤት የ24 ዓመቱ ቲክቶከር በ6 ዓመት እስር እንዲቀጣ ወስኗል
ወጣቱ ቲክቶከር ጥፋተኝነቱን አምኖ ይቅርታ ቢጠይቅም ከቅጣት ማምለጥ አልቻለም
የኡጋንዳ ፍርድ ቤት የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት እና ቤተሰቦቻቸውን የሰደበውን ቲክቶከር በእስር እንዲቀጣ ውሳኔ አሳለፈ።
ኤድዋርድ አዌብዋ የተባለው የ24 ዓመቱ ወጣት ቲክቶከር በፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ፣ ቀዳማዊት እመቤት ጃኒት ሙሴቪ እንዲሁም የፕሬዝዳንቱ ልጅ ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩግባ ዙሪያ ሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር አሰራጭቷል በሚል ነው ፍርድ ቤት የቀረበው።
ፍርድ ቤቱ ቲክቶከሩ አዌብዋ በፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ ዘመን የታክስ ጭማሪ እንደሚኖር በመግለጽ ሀሰተኛ መረጃዎችን ማካፈሉንም ሰምቷል።
የ24 ዓመቱ ወጣት ቲክቶከር ኤድዋርድ አዌብዋ ጥፋተኛ መሆኑን አምኖ ይቅርታ ጠይቋል።
ነገር ግን የኡጋንዳ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ “የ24 ዓመቱ ወጣት ቲክቶከር ኤድዋርድ አዌብዋ ምህረት እንዲደረግለት ሲለምን ለድርጊቶቹ የተጸጸተ አይመስልም፤ በቪዲዮው ላይ የተጠቀማቸው ቃላት "በእውነት ጸያፍ" ናቸው” ብለዋል።
ዋና ዳኛ ስቴላ ማሪስ አማቢሊስ "ተከሳሹ ካለፈው ታሪክ እንዲማር የሚያስችለው ቅጣት ይገባዋል" ስትል ተናግራለች።
ይህንን ተከትሎም ኤድዋርድ አዌብዋ በተከሰሰበት አራት ክሶች እያንዳንዳቸው ስድስት አመት እስር ተፈርዶበታል ነው የተባለው።