የአሜሪካ ሴኔት ቲክቶክ የማይሸጥ ከሆነ እንዲታገድ የሚያስችል ረቂቅ ህግ አጸደቀ
የአሜሪካ ህግ አውጭዎች ቻይና ቲክቶክን በመጠቀም የአሜሪካን መረጃ ልታገኝ ወይም ልትሰልል ትችላለች የሚል ስጋት እንዳላቸው ሲገለጹ ቆይተዋል
የአሜሪካ ሴኔት የቲክቶክ መተግበሪያ በቀጣይ ዘጠኝ ወራት ውስጥ የማይሸጥ ከሆነ በአሜሪካ እንዲታገድ የሚያደርገውን ረቂቅ ህግ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል
የአሜሪካ ሴኔት ቲክቶክ የማይሸጥ ከሆነ እንዲታገድ የሚያስችል ረቂቅ ህግ አጸደቀ።
የአሜሪካ ሴኔት የቲክትክ እናት ኩባንያ የሆነው የቻይናው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባይቲ ዳንስ ተወዳጁን የቲክቶክ መተግበሪያ በቀጣይ ዘጠኝ ወራት ውስጥ የማይሸጥ ከሆነ በአሜሪካ እንዲታገድ የሚያደርገውን ረቂቅ ህግ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።
የአሜሪካ ህግ አውጭዎች ቻይና ቲክቶክን በመጠቀም የአሜሪካን መረጃ ልታገኝ ወይም ልትሰልል ትችላለች የሚል ስጋት እንዳላቸው ሲገለጹ ቆይተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በሴኔቱ በጸደቀው ረቂቅ ህግ ላይ ፊርማቸውን በማስቀመጥ ህግ እንደሚያደርጉት ተናግረዋል።
በደህንነት ኮሚቴ ውስጥ ከፍተኛ የሪፐብሊካን ፓርቲ ባለስልጣን የሆኑት ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ "በአሜሪካ እጅግ ተወዳጅ የሆነውን መተግበሪያ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ለአመታት እንዲቆጣጠረው ፈቅደናል፤ ያ አደገኛ አለማስተዋል ነው" ብለዋል።
"አዲሱ ህግ የመተግበሪያው ባለቤት እንዲሸጥ ያደርጋል። ይህ ለአሜሪካ ጥሩ እርምጃ ነው።"
በአሜሪካ ውስጥ 170 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ቲክቶክ ዋሽንግተንን እና ቤጂንግን እሰጣገባ ውስጥ ካስገቧቸው የኢንተርኔት እና የቴክኖሎጂ ግንባሮች አንዱ ነው።
አፕል የሜታዎቹን ዋትስአፕን እና ትሪድስን በቻይና ካለው አፕ ስቶሩ እንዲያስወገድ በቻይና መንግስት መታዘዙን ባለፈው ሳምንት ገልጿል።
ቻይና እነዚህ መተግበሪያዎች እንዲወርዱ ያዘዘችው የብሔራዊ ደህንነት ስጋት እንዳላት በመግለጽ ነው በሏል አፕል።
ቲክቶክ የቀረበውን ረቂቅ ህግ 'በፈርስት አሜንድመንት' መሰረት እንደሚቃወመው የተገለጸ ሲሆን ተጠቃሚዎችም ጉዳዩን ወደ ህግ ሊወስዱት ይችለላሉ ተብሏል።
ባለፈው ህዳር ወር በአሜሪካ ሞንታና የሚገኝ ፍርድ ቤት ዳኛ የመናገር ነጻነትን የሚገድብ ነው በማለት ቲክቶክ እንዳይታገድ አድርገው ነበር።
የአሜሪካ የሲቪል ላይቤሪቲስ ማህበር ቲክቶክን ማገድ ወይም እንዲሸጥ ማድረግ በአምአቀፍ ደረጃ መንግስታት ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዲቆጣጠሩ በማድረግ አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ማህበሩ "አሜሪካ የውጭ ፕላትፎርሞችን ካገደች፣ ሌሎችም ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈጽሙ መጋበዝ ነው"ብሏል።
ቲክቶክ የአሜሪካን መረጃዎች ለቻይና መንግስት አለማጋራተን እና እንደማያጋራም በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በ2020 ቲክቶክ እንዲታገድ ያደረጉት ጥረት በፍርድ ቤት መታገዱ ይታወሳል። ነገርግን አዲሱ ረቂቅ ህግ የባይደን አስተዳደር ቲክቶክን ለማገድ ጠንካራ የህግ መሰረት እንዲኖራቸው ያደርጋል ተብሏል።