የቀድሞው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሀላፊ ቲክቶክን ለመግዛት ጥያቄ አቀረቡ
የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት ቲክቶክ በመላው አሜሪካ እንዲታገድ ድምጽ መስጠታቸው ይታወሳል
ቲክቶክ በአሜሪካ ብቻ 170 ሚሊዮን ደንበኞችን አፍርቷል
የቀድሞው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሀላፊ ቲክቶክን ለመግዛት ጥያቄ አቀረቡ።
የባይት ዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቲክቶክ ከሰሞኑ በአሜሪካ ሊታገድ የሚያስችል ውሳኔ ተላልፎበታል።
ይህን ተከትሎም የቀድሞው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሀላፊ ስቴቨን ሙንሽን ቲክቶክን ለመግዛት እንዳቀዱ ተገልጿል።
እንደ ቪኦኤ ዘገባ ከሆነ የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ቻይና ቲክቶክን ለመሸጥ ካልተስማማች በመላው አሜሪካ እንዳይሰራ ሊታገድ ይችላል።
ከ170 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን ደንበኞች ያሉት ቲክቶክ በአሜሪካ ከሚታገድ ይልቅ እኔ ብገዛው እና ቲክቶክ መስራቱን ቢቀጥል ጥሩ ነው ሲሉም ሙንሽን ተናግረዋል።
ቻይና አሜሪካ እንደ ቲክቶክ አይነት ኩባንያ በሀገሯ እንድታንቀሳቅስ እንደማትፈቅድም ሙንሽን ገልጸዋል።
ይሁንና ሙንሽን ቲክቶክን በምን ያህል ገንዘብ ለመግዛት እንዳቀዱ ከመናገር ተቆጥበዋል።
አሜሪካ ቲክቶክ የተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ብሄራዊ የደህንነት ስጋት ደቅኖብኛል ማለቷ ይታወሳል።
ቲክቶክ ኩባንያ በበኩሉ አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት የሚያነሱት ክስ መሰረት የሌለው፣ የማንንም መረጃ ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ ሰጥቶ እንደማያውቅ አስታውቋል።
በአሜሪካ የመታገድ እጣ ፈንታ የሚጠብቀው ቲክቶክ በሰጠው ምላሽ ቲክቶክ በአሜሪካ ቢታገድ ሶስት ሚሊዮን አሜሪካዊያን ስራ አጥ ይሆናሉ ብሏል።
ይሁንና ቲክቶክ በአሜሪካ ላለመታገድ ሲል ስለመሸጡ አልያም ስለቀጣይ እቅዱ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
አሜሪካም ቲክቶክ መረጃዋን ለቻይና አሳልፎ ስለመስጠቱ የሚያስረዳ ማስረጃ አቅርባ አታውቅም ሲል ምላሽ ሰጥታል።