አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ በ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዘገበች
አትሌት ሰንበሬ የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫውን 14 ደቂቃ 29 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዝግባለች
በውድድሩ ላይ የተሳተፉት አትሌት መልክናት ውዱ እና አትሌት ንግስቲ ሀፍቱ ደግሞ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል
አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ በጀርመን በሄርዞጌናውራች በተካሄደ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረወሰን ማስመዝገቧ ተነግሯል።
የ‘አዲዜሮ ሮድ ቱ ሪከርድስ’ ውድድር በዛሬው እለት የተካሄደ ሲሆን፤ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪም በሴቶች 5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ተሳትፋ ነበር።
አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫውን 14 ደቂቃ 29 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት አዲስ የዓለም ክብረወሰን ማስመዝገቧን ዎርልድ አትሌቲክስ አስታውቋል።
አትሌት ሰንበሬ የርቀቱን ክብረ ወሰን በእጇ ያስገባችው በቀርቡ በአትሌት ጆይሲሊን ጄፕኮስ የተያዘውን እና ገና በክብረወንነት ለመመዝገብ በሂደት ላይ የነበረውን 14:32 የሆነ ሰዓት በማሻሻል ነው።
ሰንበሬ በተጫመሪም ሴቶች ብቻ በሚወዳደሩበት ሩጫ በአትሌት ቤትሪስ ቼፕኮች ተይዞ የነበረውን 14:44 ሰዓት እና በወንዶች እና ሴቶች ድብልቅ ውድድር በአትሌት ሲፈን ሐሰን የተመዘገበውን 14:43 ሰዓት ማሻሻል ችላለች።
ስለ ውድድሩ አስተያየት የሰጠችው አትሌት ሰንበሬ፤ ደስተኛ መሆኗን ገልጻ “ከኦሎምፒክ በኋላ አዲስ የኣለም ክብረወስን በእጄ እንደማስገባ አውቅ ነበር” ብላለች።
በውድድሩ ላይ የተሳተፉት ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌት መልክናት ውዱ 2ኛ፣ አትሌት ንግስቲ ሀፍቱ ደግሞ 3ኛ ወጥተዋል።
አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ በቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ላይ ኢትዮጵያን ወክላ በ5000 ሜትር ሩጫ ተወዳድራ የነበረ ሲሆን፤ ውድድሩን 6ኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቋ ይታወሳል።