የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዣዥ ሱሄል ሁሴኒ በቤሩት መገደላቸው ተነገረ
የእስራኤል ጦር የሊባኖሱን ቡድን የሎጂስቲክ እና በጀት ሃላፊ መግደሉን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል
ሄዝቦላህ ትናንት ምሽት በእስራኤል የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) ቢሮ አቅራቢያ ለተፈጸመው የሮኬት ጥቃት ሃላፊነቱን ወስዷል
የእስራኤል ጦር የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥ የሆኑትን ሱሄል ሁሴኒ መግደሉን አስታወቀ።
ጦሩ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ የሄዝቦላህ የበጀት እና ሎጂስቲክ ክፍል ሃላፊ በቤሩት በተፈጸመ የአየር ጥቃት መገደላቸውን አመላክቷል።
ሁሴኒ ከኢራን የሚላኩ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለሄዝቦላህ የተለያዩ ወታደራዊ ክፍሎች የማከፋፈል ሃላፊነት ነበራቸው ያለው ጦሩ የሄዝቦላህ ወታደራዊ ምክርቤት አባል እንደነበሩም ጠቁሟል።
ሄዝቦላህ ሁሴኒ በቤሩት ተገድለዋል በሚል በእስራኤል ጦር የወጣውን መረጃ እስካሁን አላስተባበለም።
የሊባኖሱ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ቡድን ትናንት ምሽት በእስራኤል የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) ዋና ቢሮ አቅራቢያ ለተፈጸመው የሮኬት ጥቃት ሃላፊነቱን መውሰዱን ዩሮ ኒውስ አስነብቧል።
ዋና መሪው ሀሰን ናስራላህ የተገደሉበት ሄዝቦላህ አዲስ መሪ መምረጡንና በጋዛ ተኩስ እስካልቆመ ድረስ ከእስራኤል ጋር የሚያደርገው ውጊያ እንደማይቆም ገልጿል።
እስራኤል ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ የእግረኛ ጦሯን በማስገባት ከሄዝቦላህ ጋር የምታደርገው ውጊያ መቀጠሉን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴርም እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ድብደባ በጥቂቱ 10 የእሳት አደጋ ሰራተኞች መገደላቸውን አስታውቋል።
ሄዝቦላህ ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን በማሳየት ወደ እስራኤል መተኮስ ከጀመረ ዛሬ ጥቅምት 8 አንድ አመት ደፍኗል።
እስራኤል በጦር ጄቶቿ በቤሩትና አካባቢው የምትፈጽመው ድብደባና በደቡባዊ ሊባኖስ እየተካሄደው ያለው ውጊያ ሊባኖስን እንደ ጋዛ እንዳያፈራርሳት ስጋት ደቅኗል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሊባኖስ እያስወጡ ሲሆን፥ ቱርክም ዜጎቿን ከቤሩት ለማስወጣት 2 ሺህ ሰዎችን የሚይዙ መርከቦችን መላኳ ተሰምቷል።