የሄዝቦላህ ቀጣይ መሪ ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቁት ሀሺም ሴይፈዲን ሳይገደሉ አይቀርም ተባለ
ሀሺም ሴይዲን እስራኤል በቤሩት እያደረገች ባለው ከባድ ድብደባ መገደላቸው ነው የተነገረው
ሀሺም ሴይዲን ባሳለፍነው ሳምንት በእስራኤል የተገደሉትን የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ነስረላህን እንደሚተኩ ይጠበቅ ነበር
የሄዝቦላህ ቀጣይ መሪ ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቁት ሀሺም ሴይዲን በእስራኤል የአየር ድብደባ ሳይገደሉ አይቀርም ተባለ።
አል ዐይን ኒውስ ከእስራኤል የደህንነት ምንጭ ማረጋገጥ እንደቻው ከሆነ፤ የሄዝቦላህ ቀጣይ መሪ ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቁት ሀሺም ሴይፈዲን በቤሩት የአየር ድብደባ ተገድለዋል።
ሀሙስ ሌሊትና ትናንት አርብ በቤሩት አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ የሄዝቦላህ አመራሮችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፤ ከፍተኛ ፍንዳታዎች እንደነበሩም ታወቃል።
የእስራኤል ጦር በቤሩት የፈጸመው የአየር ድብደባ የሄዝቦህል ተተኪ አመራር ይሆል የተባለውን የሄዝቦላ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ኃላፊ ሃሸም ሴይፈዲንን ኢላማ ያደረገ እንደሆነ ተነግሯል።
የአየር ድብደባውን ተከትሎ ከትናት አርብ ጀምሮ ከሀሺም ሴይዲን ጋር ያለው ግንኙነት ተቋርጧል የተባለ ሲሆን፤ የሄዝቦላህ ከፍተኛ አማር የሆኑት ሰው በእስራኤል ድብደባ ሳይሞቱ አይቀርም ተብሏል።
ስካይ ኒውስ አረቢያ ዛሬ ጠዋት የእስራኤል የደህንነት ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ባወጣው መረጃ፤ የሄዝቦላህ ሁለተኛ ቁልፍ ሰው የሆኑት ሀሺም ሴይፈዲን መገደላቸውን አመላክቷል።
ሶስት የሊባኖስ የደህንነት ምንጮች ለሮይተርስ እንደሰጡት መረጃ ከሆነ፤ በደቡብ ቤሩት እየተካሄደ ያለው ከባድ ድብደባ የነብስ አድን ሰራተኞች ወደ ስፍራው ገብተው ያሉትን ጉዳዮች እንዳያጣሩ አግዷቸዋል ብለዋል።
አንድ የሊባኖስ የደህነንተ ምንጭ በበኩሉ፤ ከሄዝቦላህ አመራር ሀሺም ሴይፈዲን ጋር ያለው ግንኙነት ከትናነት አርብ ጀምሮ መቋረጡን ተናግረዋል።
እስራኤል ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ሌሊት በቤሩት በፈጸመችው ጥቃት የሊብኖሱ ሄዝቦላህ መሪ ሼክ ሀሰን ናስራላህን መግደሏ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የነብዩ መሀመድ የዘር ሀረግ አላቸው የሚባሉት ሀሺም ሴፌዲን የሄዝቦላህ ቀጣይ መሪ ይሆናሉ የሚለው የብዙዎችን ግምት አግኝቷል።
ሀሺም ሴይፈዲን ከናስራላህ የባሰ ደመ ሞቃት ናቸው የተባለ ሲሆን፤ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ወታደራዊ አዛዦችን ምትክ በማስመረት ቡድኑን ወደ ቀድሞ አቋሙ ሊመልሱ እንደሚችሉ ተገልጿል።
ለእስራኤል የከረረ ጥላቻ አላቸው የሚባሉት ሀሺም የሂዝቦላህ ፖለቲካ ክንፍን ሲመሩ ቆይተዋል።
ከኢራን ጋር የቀደመ እና መልካም የሚባል ግንኙነት ከመኖሩ ባለፈ በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚወደዱት ነብዩ መሀመድ ጋር የስጋ ዝምድና መኖሩ ሀሺም በቀላሉ የሂዝቦላህ መሪ ተደርገው የመመረጥ እድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆንም ተነግሮ ነበር።
የእስልምና ትምህርቱን በኢራን ያጠናው ሀሺም ከአያቶላህ ካሚኒ ጋር ጥብቅ ግንኙነትም እንዳለው ተገልጿል።
ከ64 ዓመት በፊት በሊባኖስ የተወለደው ሀሺም ከኢራናዊያን ጋር በጋብቻ ሳይቀር የተዛመደ ሲሆን ወንድ ልጁ ከአራት ዓመት በፊት በባግዳድ በአሜሪካ የተገደለው ጀነራል ቃሲም ሱሌማኒ ልጅን አግብቷል።