በህንድ በአስገድዶ መድፈር ህይወቷ ያለፈው ዶክተር ጉዳይ ቁጣን ቀሰቀሰ
ባሳለፍነው አርብ በምእራብ ቤንጋሊ የተፈጸመውን ወንጀል ተከትሎ ሴት ዶክተሮች ድርጊቱን በማውገዝ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ላይ ናቸው
በህንድ በየ15 ደቂቃ ልዩነት አንድ ሴት ተገዳ እንደምትደፈር በ2018 የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ
በህንድ በአስገድዶ መድፈር ህይወቷ ያለፈው ዶክተር ጉዳይ ቁጣን ቀሰቀሰ።
በህንድ ምእራብ ቤንጋሊ ኮልካታ ከተማ አንድ ሰልጣኝ ዶክተር በምትሰራበት የመንግስት ሆስፒታል በአስገድዶ መድፈር ህይወቷ ማለፉ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡
ለ36 ሰአታት ስትሰራ የነበረችው የ31 አመቷ ግለሰብ በስፍራው እረፈት ለማድረግ በተኛችበት ድርጊቱ መፈጸሙ ተሰምቷል፡፡
ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ በሆስፒታሉ በበጎ ፈቃደኝነት የሚገለግል አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ተቃዋሚዎቹ ፖሊስ እና የአካባቢው ባለስልጣናት ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረት አነስተኛ ነው በሚል ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
ድርጊቱ በተፈጸመበት ኮልካታ ከተማ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ከሚሰሩ ሴቶች በስተቀር በከተማዋ የሚገኙ ሁሉም ሴት ዶክተሮች እና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች በተቃውሞ ሰልፍ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከትላንት በስቲያ ጀምሮ በደልሂ፣ ሃይደራባድ፣ ቦምቤይ እና ፑኔ በተባሉ የህንድ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች በማካሄድ ላይ ሲሆኑ ዛሬን ጨምሮ በመጪዎቹ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በመላው ሀገሪቱ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ጥሪ እየተደረገ ነው፡፡
ህንድ ከፍተኛ የአስገድዶ መድፈር ምጣኔ ካለባቸው ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች፡፡
በሀገሪቱ የቡድን አስገድዶ መድፈሮችን ጨምሮ ሌሎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ከፍተኛ እንደሆኑ ይነገራል፡፡
በፈረንጆቹ 2012 በተመሳሳይ የ23 አመቷ ወጣት በቡድን ተደፍራ ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ የሀገሪቱ መንግስት በወንጀለኞች ላይ ከባድ ቅጣት ለማስተላለፍ የህግ ማሻሻያዎችን ቢያደርግም የሴቶች መብት ተሟጋቾች ቅጣቱ በቂ አይደለም በሚል ይሞግታሉ፡፡
እንደ ሀገሪቱ ወንጀል ምዝገባ ቢሮ መረጃ ከሆነ በ2012 በህንድ 25 ሺህ ሴቶች ተገደው ሲደፈሩ በ2018 ይህ ቁጥር ወደ 39 ሺህ አድጓል፡፡
በ2018 የነበሩ መረጃዎች በህንድ በየ15 ደቂቃ ልዩነት አንድ ሴት ተገዳ እንደምትደፈር የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
በ2020 በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይህ ቁጥር ወደ 30 ሺህ ዝቅ ማለት ቢችልም ሀገሪቱ አሁንም ከፍተኛ የአስገድዶ መድፈር ምጣኔ ካለባቸው ሀገራት ተርታ ትገኛለች፡፡
መንግስት ባሻሻለው ህግ የአስገድዶ ደፋሪዎች ከ10 – 16 አመት እና ከዛ በላይ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ጥቃት የተፈጸመባት ሴት እድሜዋ ከ12 አመት በታች ከሆነ ደግሞ ጥፋተኛው በሞት እንዲቀጣ ደንግጓል፡፡
በህንድ የሚንቀሳቀሱ የሴቶች መብት ተሟጋቾች የሀገሪቱ ፖሊስ እና የፍትህ ተቋማት በአስገድዶ ደፋሪዎች ላይ የሚወስዱት እርምጃ አነስተኛ መሆን እና ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አለመስጠታቸው ወንጀሉ እንዱጨምር ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ከ2018-2022 ባሉት አመታት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ከፈጸሙ ግለሰቦች መካከል በህግ ተጠያቂ የተደረጉት 28 በመቶ ያህሉ ናቸው ፡፡