በአንድ ቀን 15 የአለም ክብረወሰኖችን የሰበረው አሜሪካዊ
“ሪከርድ ሰባባሪው” የሚል ቅጽል ስም የወጣለት ዴቪድ ራሽ በለንደን የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ዋና ቢሮ በመገኘት አዳዲስ ክብረወሰኖችን አስመዝግቧል
ዴቪድ እስካሁን 250 የአለም ክብረወሰኖችን በመስበር ስሙን በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ አስፍሯል
አሜሪካዊው ዴቪድ ራሽ 15 የአለም ክብረወሰኖችን በአንድ ቀን ማስመዝገብ መቻሉ ተነገረ።
ዴቪድ ከሰሞኑ በለንደን ወደሚገኘው የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ዋና ቢሮ በመገኘት ነው ክብረወሰኖቹን የሰበረው።
“ሪከርድ ሰባባሪው” የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ዴቪድ አዳዲሶቹን ሪከርዶች ሲሰብር “ከረሜላ በመስበር ላይ ይመስል በጣም ቀሎት ነበር” ይላሉ ክብረወሰኖቹ መሰበራቸውን ያረጋገጡት ዊል ሲንደን።
ዴቪድ ሶስት አፕሎችን በእጁ እየተወረወረ በመቅለብና በጥርሶቹ በመጋጥ አዲስ ክብረወሰን ይዟል፤ በአንድ ደቂቃ አፕሎቹን 198 ጊዜ በመጋጥ።
የጠረጼዛ ቴኒስ ኳሶችን በሁለት ኩባያዎች ላይ በማንጠባጠብም አዲስ ክብረወሰን ይዟል።
ሪከርድ የሚከተለው አሜሪካዊ የቤዝቦል ኳስ በእጁ መዳፍና አይበሉባ በማንጠርም ሪከርድ ሰብሯል።
ዴቪድ ራሽ በ30 ሰከንድ ውስጥ የጠረጼዛ ቴኒስ ኳስን በአፉ በመያዝና ከግድግዳ ጋር በፍጥነት በማላተም ተይዞ የነበረውን ክብረወሰንም ሰብሯል ይላል የአለም የድንቃድንቅ መዝገብ በድረገጹ።
በ30 ሰከንድ ውስጥ በርካታ ቲሸርቶችን በመልበስ እና አንድ ሊትር የሎሚ ጭማቂ በስትሮ በመጠጣት ተይዘው የነበሩ ክብረወሰኖችንም ሰብሯል።
በአንድ ቀን በድምሩ በ15 ክብረወሰኖችን የሰበረው ዴቪድ ራሽ 250 የአለም ክብረወሰኖችን በመስበር ስሙን በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ አስፍሯል።
ራሽ በቀጣይም በሌሎች ዘርፎች “ፈታኙን” ክብረወሰን የመስበር ጥረት እንደሚቀጥል ነው ያስታወቀው።
አንዳንዶቹ የሰበራቸው ክብረወሰኖች ቀላል ቢመስሉም ከወራት እስከ ሳምንታት የፈጀ ልምምድ እንዳደረገ በመግለጽም ስኬት ያለጥረት እንደማይመጣ ተናግሯል።