በፈጣን የጽሁፍ ክህሎቱ የሚታወቀው ህንዳዊ በተለያዩ ዘርፎች ስሙን በድንቃ ድንቅ መዝገብ አስፍሯል
በአፍንጫው የሚጽፈው ህንዳዊ የራሱን ክብረወሰን ለሶስተኛ ጊዜ ሰበረ።
የ44 አመቱ ቪኖድ ኩማር ቻውድሃሪ ኮምፒውተር ላይ በአፍንጫው በፍጥነት በመጻፍ ነው የራሱን ክብረወሰን ያሻሻለው።
ቻውድሃሪ 26ቱንም የላቲን ፊደላት በ27.80 ሰከንድ በመጻፍ ነበር በ2023 ለመጀመሪያ ጊዜ ስሙን በድንቃድንቃ መዝገብ ማስፈር የቻለው።
በሁለተኛው ሙከራውንም በ26.73 ሰከንዶች ጽፎ በማጠናቀቅ የራሱን ክብረወሰን ማሻሻል ችሎ ነበር።
ቻውድሃሪ ከሰሞኑም ሁሉንም የላቲን ፊደላት በመሃላቸው ክፍተት እየተወ በ25.6 ሰከንዶች በአፍንጫው በመጻፍ ክብረወሰኑን ማሻሻሉን የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ በኤክስ ገጹ ላይ አስፍሯል።
በጽሁፍ ክፍሎቱ “የህንዱ ጸሃፊ” የሚል ተቀጽላ እንደተሰጠው የሚናገረው ቻውድሃሪ፥ ባሻገር የላቲን ፊደላትን ከኋላ ወደ ፊት (ከዜድ ወደ ኤ) በአንድ እጁ በፍጥነት (በ5.36 ሰከንድ) በመጻፍም ስሙን በአለማቀፉ መዝገብ ማስፈር ችሏል።
“የጽሁፍ ስራ መተዳደሪያ ነው፤ ለዚያም ነው በጽሁፍ የተለያዩ የአለም ክብረወሰኖችን ለመስበር የምሞክረው፤ ጉዳዩ እንጀራዬም የአዳዲስ ክብረወሰኖች ማስመዝገብ ፍላጎቴ ማሳኪያም ሆኗል” ይላል የ44 አመቱ ጎልማሳ።
በአፍንጫው በመጻፍ ክብረወሰኑን ለማሻሻል በየቀኑ ለስአታት እንደሚለማመድ ቻውድሃሪ “አቀርቅሮ መጻፍ አድካሚና አንዳንዴም ኮከቦችን መመልከት ያስከትላል” ሲል ያብራራል።
ሁሉም ነገር በልምምድ እንደሚሳካም በመጥቀስም እንደቀድሞው የክሪኬት ዝነኛ ተጫዋች ሳቺን ቴንዱልካር በርካታ ክብረወሰኖችን የመስበር ፍላጎት እንዳለው መግለጹን ኤንዲቲቪ አስነብቧል።