ለረጅም ሰአታት ምግብ በማብሰል የአለም ክብረወሰን ሰብሬያለሁ በሚል ሲያጭበረብር የነበረው ሼፍ ታሰረ
ጋናዊው ወጣት ከጊነስ ቡክስ ተሰጥቶኛል ያለውን ሀሰተኛ ምስክር ወረቀት በማሳየት ከተለያዩ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ አግኝቷል ተብሏል
ጋናውያን የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ሪከርድን ለመስበር የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ይታወቃሉ
አቤኔዘር ስሚዝ የተባለው ጋናዊ ምግብ አብሳይ (ሼፍ) ለ802 ሰአታት ከ25 ደቂቃ ያለማቋረጥ ምግብ በማብሰል የአለም ድንቃድንቅ መዘገብ ሪከርድ መጨበጡን ያስታወቀው ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ነበር፡፡
ወጣቱ ሼፍ ለረጅም ሰአታት ምግብ በማብሰል የሪከርዱ አዲስ ባለቤት መሆኑን ከመግለጽ ባለፈ በራሱ ያሰራውን ከአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ተሰጥቶኛል ያለውን የምስክር ወረቀት ለማረጋገጫ ይዞ ቀርቧል፡፡
መረጃው የደረሰው የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ በቃል አቀባዩ በኩል ባወጣው መግለጫ አቤኔዘር ስሚዝ ያቀረበው ምስክር ወረቀት ሀሰተኛ መሆኑን እና የሪከርዱ ባለቤት ነኝ ብሎ ያሰራጨው መረጃም እውነት እንዳልሆነ አረጋግጧል፡፡
ወጣቱ ባሳለፍነው መጋቢት ወር በዋና ከተማዋ በሚገኝ የገበያ ማዕከል ለረጅም ሰአታት በማበሰል ሪከርዱን ለማሻሻል ሙከራ ሲያደርግ በጋናውያን የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች ዘንድ እውቅናን አግኝቶ ነበር፡፡
ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የሪከርዱ ባለቤት እንደሆነ በመናገር ከተለያዩ ስፖንሰሮች ገንዘብ ሲቀበል ነበር የተባለው አቤኔዘር፥ ከስፖንሰር አድራጊዎቹ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የሪከርድ ባለቤትነቱን ለማወጅ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አጭበርባሪ መሆኑ ተደርሶበታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን እስካሁን ምንም አይነት ክስ እንዳልመሰረተበት ተሰምቷል፡፡
ጋናውያን ክብረወሰን በመስበር ስማቸውን በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ለማስፈር የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ይታወቃሉ፡፡
በቅርቡ የታማላ ከተማ ነዋሪዋ ፋይላቱ አበዱራዛቅ የተባለች ሴት ያለማቋረጥ ለረጅም ሰአታት ምግብ በማበሰል ሪከርዱን ለመስበር ሙከራ ያደረገች ሲሆን ባለፈው አመት ደግሞ አፉዋ አሳንቲዋ የተባለች ጋዜጠኛ ለረጅም ሰአት በመዝፈን ሪከርዱን ለመያዝ ሙከራ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለረጅም ሰአት ምግብ የማብሰል ሪከርዱን ይዞ የሚገኘው አየርላንዳዊው ሼፍ አለን ፊሸር ነው፡፡
ፊሸር ከዚህ ቀደም ናይጄሪያዊቷ ሼፍ አስመዝግባው የነበረውን 93 ሰአት ከ11 ደቂቃ ሪከርድ ወደ 119 ሰአት ከ57 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ በማሻሻል የሪከርዱ ባለቤት መሆን ችሏል፡፡