በረጅም ጥፍር ባለቤትነት በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ የሰፈረችው አሜሪካዊት ተፎካካሪ እየተፈለገላት ነው
የአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ለ27 አመታት ጥፍሯን ባለመቆረጥ ደረጃውን ይዛ የምትገኝውን እንስት መፎካከር የሚችሉ ሰዎች ማመለከቻቸውን እንዲያስገቡ ጠይቋል
የሪከርዱ ባለቤት አሜሪካዊት የአስሩም ጣቶቿ ጥፍሮች አጠቃላይ እርዝመት 13 ሜትር ደርሷል
ለ27 አመታት ጥፍሯን ባለመቆረጥ በአለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ባለ ረጅም ጥፍር ባለቤት በሚል የተመዘገበችው ዲያና አርምስትሮንግ ተፎካካሪ እየተፈለገላት ነው፡፡
በ2022 የሪከርድ ባለቤትነቱን ከአለም ድንቃድንቅ መዝገብ የተረከበችው ዲያና ጥፍሯን ሳትቆረጥ 27 አመታትን አስቆጥራለች፡፡
ጊነስ ወርልድ ሪከርድ በኢንስታግራም ይፋዊ ገጹ ላይ የዲያናን ሪከርድ የምትገዳደሩ ከየት አላችሁ ሲል ጥሪ ማቅረቡን ሚረር ዘግቧል፡፡
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1997 ጀምሮ ጥፍሯን ማሳደግ እንደጀመረች የምትናገረው ዲያና ብዙዎች የጥፍሯን ተፈጥሯዊነት በመጠራጠር በርካታ ጥያቄዎችን እንደሚጠይቋት ትናገራለች፡፡
መሬት ላይ የሚጎተቱት ጥፍሮቿ በእለት ከእለት ኑሮዋ ላይ ያለው ተጽእኖ በተለይ ሰውነቷን ስትታጠብ ፣ ስትመገብ እና ስትተኛ የሚኖረውን ተጽእኖ በተመለከተ ከሰዎች በበዛት ከሚቀርቡላት ጥያቄዎች መካከል ሲሆኑ ማሳደግ ስትጀምር ጥፍሮቿ እዚህ ደረጃ ይደርሳሉ የሚል እምነት እንዳልነበራት ታነሳለች፡፡
ጥፍሯን ካለመቆረጥ ውሳኔዋ ጀርባ የ16 አመት ልጇ አሟሟት ምክንያት መሆኑን የምትናገረው ዲያና “ልጄን ያጣኋት በ1997 በድንገት ነው፤ በየሳምንቱ የጥፍሬን ንጽህና የምትንከባከብልኝ እና የጥፍር ቀለም የምትቀባኝ ሟቿ ልጄ ነበረች፤ በድንገት ያጣኋትን ልጄን ለማስታወስ መቆረጥ ያቆምኩት ጥፍር አሁን ላይ የአለም ሪከርድ ባለቤት አድርጎኛል” ብላለች፡፡
በ2022 በድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስትመዘገብ የአስሩም ጣቶቿ ጥፍሮች ርዝመት 13 ሜትር ሲሆን እድገቱ አሁንም እንዳላቆመ የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ በቅርቡ ይፋ ባደረገው የኢንስታግራም ገጽ ልጥፉ ላይ ጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የጥፍሮቿ ርዝመት በተለምዶ “ስኩል ባስ” በመባል ከሚታወቀው ቢጫ የተማሪዎች አውቶብስ እንደሚበል ያስታወቀው የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ የዲያናን ሪከርድ ለመፎካከር የሚያስችል ተፈጥሮ ያላቸው ሰዎች ማመልከቻቸውን እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡