ከቀናት በኋላ ይፋ የሚደረገው አይፎን 16 ምን አዳዲስና የተለዩ ነገሮችን ይዟል?
ከጉግል ፒክስልና ከሳምሳንግ ጋር ፉክክር ላይ የሚገኝው አፕል በአዲሱ ምርቱ ሰውሰራሽ አስተውሎት ላይ ትኩረት ማድረጉ ተሰምቷል
አፕል በአይፎን 16 በሚያቀርባቸው አራት ሞዴሎች መጠናቸው ሰፋ ያሉ ስክሪኖችን እንደሚጠቀም ተነግሯል
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል በተከታታይ እያመረታቸው በሚገኙት በአይፎን ምርቶቹ አዲስ የሆነውን አይፎን 16 በመጪው ሳምንት ሰኞ ያስተዋውቃል።
ከአይፎን 16 እስከ አይፎን 16 ፕሮማክስ በአራት ሞዴሎች ለገበያ ይቅርባሉ የተባሉት ስማርት ስልኮች ከ6.1 እስከ 6.9 ኢንች ስክሪን ስፋት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
ስልኮቹ ለገበያ በሚቀርቡበት ወቅት ተመሳሳይ ሞዴል ያለው የአፕል ስማርት ዋቾ አብሯቸው ለገበያ እንደሚቀርብም ነው የተገለጸው።
ጎግል ፒክስል በቅርቡ ለገበያ ካቀረባቸው ፒክስል 9 እና ፒክስል ፕሮ ስልኮች በሶፍትዌሩ ውስጥ ባካተታቸው የሰውሰራሽ አስተውሎት አገልግሎቶች ከፍተኛ ውድድር እንደሚጠብቀው የተነገረው አይፎን ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በሰፊው ጥቅም ላይ ለማዋል ሙከራ ማድረጉ ተነግሯል።
ከቻትጂፒቲ ጋር በፈጸመው ስምምነት በአዲሱ የአይፎን 16 ስልኮቹ ላይ ድምጽን በመጠቀም መልዕክቶችን መጻፍ ፣ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማዘዝ እና ከፎቶ ላይ አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማውጣት የሚያግዝ አሰራር እንዳለው ነው የተነገረው።
አዲሶቹ የአይፎን ምርቶች በ128 ፣ 256፣ በ512 ጂቢ እና እስከ አንድ ቴራባይት ድረስ ፋይሎችን የመያዝ አቅም እንደሚኖራቸው ሲነገር የሚወጣላቸውም ዋጋ ከዚሁ ፋይል በመያዝ መጠናቸው እና ከሞዴል አይነታቸው ጋር እንደሚለያይ ተሰምቷል።
አፕል በሳምሳንግ ምርቶች እየተወሰደበት የሚገኝውን የካሜራ ጥራት ብልጫ ለማሻሻል ባደረገው ጥረት ስልኮቹ 5X ቴሌፎቶ ካሜራ የተገጠመላቸው ሲሆን በአይፎን 16 ፕሮ ላይ 49 ሜጋ ፒክስል ፎቶዎችን በጥራት ማንሳት የሚችል አልትራ ዋይድ ካሜራ ተገጥሞለታል ነው የተባለው።
ከዚህ ባለፈም የሰዎችን ዘመናዊ ፎቶ የማንሳት እና ቪድዮ የመቅረጽ ልምድ ለማሳደግ በውጨኛው የስልኩ አካል ላይ ፎቶ ማንሳት የሚያስችል ቁልፍ (በተን) ይኖራቸዋል ተብሏል።
አፕል አዳዲሶችን ስልኮች እንደየሞዴላቸው በተለያየ አይነት የቀለም አማራጭ የሚያቀርብ ሲሆን ግራጫ፣ ነጭ፣ ሰማያዊ፣ ሮዝ፣ ጥቁር እና ብራማ ቀለም በስፋት ከሚመረቱባቸው ቀለሞች መካል ይጠቀሳሉ።
በመጪው ሰኞ በይፋ አዳዲሶችን የአይፎን ሞዴሎች የሚስተዋውቀው አፕል ከ11 ቀናት በኋላ በፈረንጆቹ መስከረም 20 ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።