ቮልቮ በ2030 ሙሉ ለሙሉ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ለማምረት የያዘውን እቅድ ሰረዘ
ኩባንያው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ተፈላጊነት ቀንሷል በሚል ነው
ባሳለፍነው ሀምሌ ወር በአውሮፓ ሀገራት የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ተፈላጊነት በ11 በመቶ ቀንሷል
ከትናንሽ እስከ ከባድ የጭነት ተሸከርካሪዎችን በማምረት የሚታወቀው ቮልቮ በ2030 ሙሉ ለመሉ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለማምረት የያዘውን እቅድ መሰረዙን አስታወቀ፡፡
ኩባንያው ወደ ኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች አምራችነት ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር እቅድ መያዙን ያስታወቀው ከሶስት አመታት በፊት ነበር፡፡
ቮልቮ አሁን ባለው የተሸከርካሪዎች ገበያ የኤሌክትሪክ መኪኖች ያላቸው ተፈላጊነት ማሽቆልቆል እቅዱን እንዲከልስ ምክንያት እንደሆነው አስታውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በቻይና የሚመረቱ የኩባንያው ተሸከርካሪዎች በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ ገበያ የተጣለባቸው የታሪፍ ጭማሪ በትርፍ ምጣኔው ላይ እክል መፍጠሩን ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ካናዳ ከቻይና በሚመጡ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ላይ የ100 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
ቮልቮ የአካበቢ ጥበቃ ላይ ለመሳታፍ ታዳሽ ሀይል የሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎችን ከሚያመርቱ ጄነራል ሞተርስ እና ፎርድ ኩባንያዎች ጋር ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ ያለውን አለምቀፋዊ ፍላጎት መነሻ በማድረግ እስከ 2030 ድረስ የኤሌክትሪክ እና የነዳጅ ሀይል የሚጠቀሙ (ሀይብሪድ) መኪኖችን እያመረተ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቀው፡፡
የስዊድኑ የመኪና አምራች በቻይና ፣ ቤልጄየም እና አሜሪካ ማምረቻዎች አሉት፡፡
የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጂም ሮውን የወደፊቱ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ የኤሌክትሪክ ሀይል ከሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎች ጋር መቆራኝቱ አይቀርም፤ ነገር ግን የምርቱ ገዢዎች እና ምርቱ በተመሳሳይ ፍጥነት መጓዝ ካልቻሉ ኪሳራን ሊያሰከትል ይችላል ብለዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው ተሸከርካሪዎቹ በስፊው በገበያ ውስጥ ገብተውባቸው በነበሩባቸው ያለፉት አመታት ሰፊ የገበያ ፍላጎት ቢኖራቸውም ፤ የቻርጅ ማድረጊያ መሰረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ አለመሟላት እና ለገዢዎች ይደረጉ የነበሩ ማበረታቻዎች መነሳታቸው ፍላጎቱ እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
ታዋቂው የአሜሪካ መኪና አምራች ፎርድ በተመሳሳይ ከኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ጋር በተገናኘ የያዛቸውን እቅዶች በመከለስ ላይ ነው፡፡
ኩባንያው ለገበያ ሊያቀርባቸው የነበሩ ፒካፕ እና የቤተሰብ መኪኖችን የሚያስተዋውቅበትን ጊዜ አራዝሟል፡፡
እንደ አውሮፓ አውቶሞቢል አምራቾች መረጃ ከሆነ ባሳለፍነው ሀምሌ ወር በአውሮፓ ህብረት ሀገራት የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ተፈላጊነት በ11 በመቶ ቀንሷል፡፡