በአማራ ክልል ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ጾታዊ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን ቢሮው ገለጸ
በ2016 ብቻ 1324 ጾታዊ ጥቃቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገልጿል
ኢሰመኮ ሳምንት ባወጣው ሪፖርት ከሀምሌ 2016 እስከ ጥቅምት 2017 በአማራ ክልል 200 ጾታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን መግለጹ ይታወሳል
በአማራ ክልል ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ጾታዊ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ በፌደራል መንግስት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ በሚገኘው በትጥቅ የታገዘ ግጭት መነሾ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል ብሏል ቢሮው።
በቢሮው የሴቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ባለሙያ አስናቀ ለውየ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰበት ከ2013 ጀምሮ ከግጭት እና ጦርነት ጋር በተያያዘ ክልሉ የሰብአዊ ጥቃት እና የአስገድዶ መድፈር ሰለባ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ከ2015 ጀምሮ እስካሁን በቀጠለው ግጭት ደግሞ ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተገናኘ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ቁጥራቸው እያደገ እንደሚገኝ ነው የነገሩን፡፡
በ2016ዓ.ም ከ1324 በላይ ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን በ2017 ሩብ አመት ደግሞ ከ131 በላይ ጾታዊ ጥቃቶች ተመዝግበዋል ብለዋል አቶ አስናቀ።
ኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት አስመልክቶ ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት ከሀምሌ 2016 እስከ ጥቅምት 2017 በአማራ ክልል 200 ጾታዊ ጥቃቶች መደረሳቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ባለፉት አመታት በአማራ ክልል የሚፈጸሙ የአስገድዶ መድፈሮችን ለመቀነስ በተሰራው ስራ ከፍተኛ ለውጥ እና መሻሻል ታይቶ እንደነበር የሚያነሱት አቶ አስናቀ፤ ግጭት ባልነበረባቸው ጊዜያት በሩብ አመት ውስጥ ይህን ያህል ከፍተኛ የጥቃት ቁጥር ተመዝግቦ አያውቅም ይላሉ፡፡
ጥቃቱ የሚፈጸመው በማን እንደሆነ የጠየቅናቸው አቶ አስናቀ ሲመልሱ “መረጃዎችን ባሰባሰብንባቸው ስፍራዎች ከተጠቂዎቹ ያገኘነው መረጃ የሚያሳየው የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ታጣቂዎች እንዲሁም በአካባቢው በሚኖረው የማህበረሰብ አባላት እንደሚፈጸም ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከሚደርስባቸው ስነልቦናዊ እና ማህበራዊ ተጽዕኖ አንጻር ወደ ህክምና ተቋማት ስለማይመጡ እንዲሁም ግጭቱ አሁን ከሚገኝበት ሁኔታ አንጻር በሁሉም አካባቢዎች ተዘዋውሮ መረጃዎችን ለመሰብሰብ አስቸጋሪ በመሆኑ የተጠቀሰው ቁጥር መሬት ላይ ያለውን ትክክለኛ መጠን አይገልጽም ተብሏል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ደብረ ታቦር፣ ደቡብ ጎንደር ፣ ባህርዳር እና ደብረብርሀን ከፍተኛ ጾታዊ ጥቃቶች ከተመዘገቡባቸው የክልሉ አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ምስራቅ ጎጃም ፣ ምእራብ እና ሰሜን ጎጃም ጦርነቱ ከሚገኝበት ሁኔታ አንጻር ቢሮው የተጠናከሩ መረጃዎች ባይኖሩትም በነዚህ ስፍራዎች የሚኖሩ ሴቶች እና ህጻናት ለከፍተኛ ጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸወን ቢሮው መረጃዎች እንደሚደርሱት ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
“ሴቶች ጾታዊ ጥቃት ደረሶብናል ብለው ወደ ተቋማት አለመምጣታቸው አሁንም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እና የችግሩን አስከፊነት በውል ለመገንዘብ አዳጋች አድርጎብናል” የሚሉት አቶ አስናቀ ቢሮው ከሌሎች የሀገር ውስጥ እና የውጭ አጋዥ አካላት ጋር በመሆን የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴቶች የህግ ፣ የጤና እና የስነልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ አስናቀ ከሴቶች በተጨማሪ በጦርነቱ ምክንያት ህጻናትም ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሴቶች እና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በዳሰሰበት አመታዊ ሪፖርቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በቀጠሉ ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች ከ5ሺህ የሚልቁ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የመማር ማስተማር ሂደቱ መቋረጡን ይፋ አድርጓል፡፡
በስምንት ክልሎች ከተዘጉት ከ5 ሺህ በላይ ት/ቤቶች ውስጥ ከ4ሺህ በላይ የሚሆኑት በአማራ ክልል እንደሚገኙም በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
በዚህም ምክንያት ቁጥራቸው የበዛ ሕጻናትና ሴቶች ተፈናቅለው ወደ ከተማ መግባታቸውን፣ለጉልበት ብዝበዛ እና ያለእድሜ ጋብቻ መጋለጣቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በበኩሉ መስከረም ወር ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በክልሉ መመዝገብ ከነበረባቸው 7 ሚሊየን ተማሪዎች መካከል እስከ መስከረም 8 የተመዘገቡት 2 ሚሊየን 295 ሺህ 150 (32 በመቶ) ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡
አቶ አስናቀ እንዳሉት “በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች በተገቢውነ ሁኔታ እየሰሩ" ባለመሆናቸው እና ጦርነቱ በፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ጫና ምክንያት ወላጆች ልጆቻቸውን ያለ እድሜያቸው እንዲሰሩ እና ትዳር እንዲመሰርቱ እያደረጉ ናቸው።
አቶ አስናቀ አክለውም "በአንዳንድ ቦታዎች ትምህርት የተቋረጠባቸው ታዳጊዎች እና ወታጣች ታጣቂዎችን ለቀላቀል መገደዳቸውን መረጃዎች እየደረሱን ነው" ብለዋል። አል ዐይን አማርኛ ይህን መረጃ ማረጋገጥ አልቻለም።
በአማራ ክልል መንግስት በይፋ የአስቸኳይ ጊዜ ካወጀበት ከሀምሌ 2015 ጀምሮ በሚደረጉ ውጊያዎች በንጹሃን ላይ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና ጅምላ እስራት እየተፈጸሙ መሆናቸውን ኢሰመኮን ጨምሮ አለምአቀፍ የመብት ተቋማት ሪፖርት አድርገዋል።
በአትዮጵያ ከሁለት አመታት ለተሻገረ ጊዜ በቆየው የሰሜኑ ጦርነት ወቅት በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በግጭቱ ተሳታፊ ባልነበሩ ብዙ ሴቶች ለተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች መጋለጣቸው ይታወሳል።
ስለሴቶች ጾታዊ ጥቃት አለምአቀፍ ጥናቶች
የተመድ የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በቅርቡ ባወጣው መረጃ በመላው አለም ከ370 ሚሊየን በላይ ሴቶች ከ18 አመታቸው በፊት ተደፍረዋል አልያም ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡
ዩኒሴፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በችግሩ ዙሪያ አደረግኩት ባለው አለማቀፍ የዳሰሳ ጥናት ከስምንት ሴቶች አንዷ ከ18 አመቷ በፊት ተደፍራለች ወይም ጾታዊ ጥቃት ይደርስባታል ያለ ሲሆን፤ ከስሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የጾታዊ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው ውስጥ በቀዳሚነት ተቀምጠዋል።
79 ሚሊየን ሴቶችና ልጃገረዶች (22 በመቶ) የጥቃቱ ተጋላጭ ናቸው ብሏል ጥናቱ።