ሼህ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አልነሃያ እና ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ በስልክ መከሩ
ሼህ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አልነሃያን ለጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ “የእንኳን ደስ አልዎት መልእክት” አስተላለፉ
“ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች”ም መሪዎቹ ከተወያዩባቸው ዓበይት አጀንዳዎች ናቸው
የአቡዳቢ አልጋወራሽና የየተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (ዩኤኢ)ምክትል የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሼህ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አልነሃያን ለጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ እንኳን ደስ አልዎት መልእክት አስተላለፉ፡፡
ሼህ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ይህንን ያሉት ከጠቅላይ ሚኒሰትር ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ነው፡፡
ሼህ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ዐቢይ አህመድ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሰትር ሆነው መመረጣቸው ደስተኛ መሆናቸውና መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ ማለታቸውን የኤሚሬትስ ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
መሪዎቹ በስልክ ባደረጉት ውይይት የዩኤኢ-ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር ለማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል፡፡
ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችም መሪዎቹ በስልክ በነበራቸው ቆይታ ከተወያዩባቸው ዓበይት አጀንዳዎች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ፓርላማ በትናንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒሲትሩ የቀረበውን ሰባት ሴቶችን ያካተተ የካቢኔ ሹመት ማፀደቁ ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚነሲትሩ ከሸሟቸው 22 ሚኒሰትሮች ሶስቱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መወከላቸው አዲሱ መንግስት የወሰደው መልካም እርምጃ ነው ተብሎለታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮችን ነው የካቢኔያቸው አባላት ያደረጉት፡፡
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር በለጠ ሞላ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀመንበር ቀጄላ መርዳሳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አባላቱ በመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነቶች ላይ እንዲሠሩ የሚያስችለውን ውሳኔ ከሰሞኑ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ የአዲስ አበባ ከተማ ኢንቨስትመንትን ኮሚሽነር ሆነው ርክክብ አድርገዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጣሂር መሐመድ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የንቅናቄው ምክትል ሊቀመንበር የሱፍ ኢብራሂም የአዲስ አበባ ከተማ ንብረት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ በመሆን መሾማቸው ይታወሳል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ የኦሮሚያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾማቸውም አይዘነጋም፡፡በቅርቡ ሁሉን አካታች የሆነ ብሄራዊ የምክክር መድረክ ማካሄድ እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መናገራቸውም ይታወሳል፡፡