ዩኤኢ ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ፓርላማ ያሳለፈውን ውሳኔ ውድቅ አደረገች
ውሳኔው በሰብዓዊ መብቶች ዘርፍ ለተገኙ ስኬቶች እውቅና ለመስጠት ያልፈለገ ስትልም ነው ዩኤኢ ያስታወቀችው
ዩኤኢ ትክክል እንዳልነበሩ ጭምር ተነጋግረን ውድቅ ያደረግናቸውን ሃሳቦች ጭምር ያካተተ ነው ያለችውን ውሳኔ አጥብቃ እንደምትቃወም አስታውቃለች
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) የአውሮፓ ፓርላማ በዚህ ሳምንት ያሳለፈውን የውሳኔ ሃሳብ እንደማትቀበል አስታወቀች፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰብዓዊ መብቶች ዳይሬክተር ሰዒድ አል ሃብሲ ውሳኔውን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ከአሁን ቀደም ተነጋግረን ትክክል አልነበሩም በሚል ውድቅ ያደረግናቸውን ጉዳዮች ያካተተውን ውሳኔ አጥብቀን እንቃወማለን ሲል የሚያትተው መግለጫው ዩኤኢ በሰብዓዊ መብቶች ዘርፍ ላስመዘገበቻቸው ስኬቶች እውቅና እንደነፈገም ይጠቁማል፡፡
“ዩኤኢ ከሃገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጥበቋን ትቀጥላለች”- ልዑል አልጋወራሽ መሃመድ ቢን ዛይድ
እያንዳንዱ ሃገር የራሱ ህግና ተቋማት አሉት የሚልም ሲሆን የዩኤኢ ህገ መንግስት እና ሌሎች ብሔራዊ ህግጋቶች ሁሉም ዜጎች እና ነዋሪዎች በፍትሐዊነት የሚታዩባቸውን መሰረታዊ መብቶች መደንገጋቸውን ይገልጻል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን በብሔራዊ ደረጃ ማቋቋሟ በሃይማኖት ነጻነት እና በመቻቻል ለሌሎች መነሳሻ ሊሆን በሚችል ደረጃ ተጠቃሽ እንዳደረጋትም ነው መግለጫው የሚጠቅሰው፡፡
የኮሚሽኑ መቋቋም የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የሰላም፣ የወንድማማችነት እና የፍቅር እሴቶችን ለማጎልበት ያላትን ቀጣይ ፍላጎት የሚያሳይ ነውም ብሏል፡፡
የሃይማኖት፣ የእምነት፣ የቋንቋ እና የብሔር ልዩነቶች ሳይገድቡ አብሮ የመኖር እና የወንድማማችነት ሰብዓዊ አስፈላጊነት ላይ ዩኤኢ ያላትን መልዕክት ስለማካተቱም ነው መግለጫው የሚያስቀምጠው፡፡