በሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት የደረሰባት መርከብ ሰጠመች
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ ቀደም ሲል መርከቧ ጥቃት በደረሰባት ወቅት 41ሺ ቶን ማዳበሪያ ተሸክማ እንደነበር መግለጹ ይታወሳል
መርከቧ በደቡባዊ ቀይ ባህር መስጠሟን አለምአቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግስት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል
በሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት የደረሰባት መርከብ ሰጠመች።
ባለፈው ወር በሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት የደረሰባት 'ዘ ሩቢይማር' የተሰኘችው እቃ ጫኝ መርከብ በደቡባዊ ቀይ ባህር መስጠሟን አለምአቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግስት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ይህ እውነተኛነቱ ከተረጋገጠ፣ የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ከጀመሩበት ከባለፈው ህዳር ወር ወዲህ የመጀመሪያው የመስጠም አደጋ ይሆናል።
መርከቧ አርብ እለት ማታ መስጠሟን ያስታወቀው መግለጫ አካባቢያዊ አደጋ እንዳይከሰት አስጠንቅቋል።
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ ቀደም ሲል መርከቧ ጥቃት በደረሰባት ወቅት 41ሺ ቶን ማዳበሪያ ተሸክማ እንደነበር መግለጹ ይታወሳል።
የሀውቲ ታጣቂዎች ከባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ወዲህ በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ጥቃት የሚያደርሱት፣ ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ለፍልሴጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋርነት ለማሳየት መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ሰኞ እለት ንብረትነቷ የዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) የሆነውን ይችን መርከብ የጎበኘው የየመን መንግስት ቡድን፣ በከፊል መስጠሟን እና በጥቂት ቀናት ውስጥ ልትሰጥም እንደምትችል ገልጾ ነበር።
ቀደም ሲል የአሜሪካ መንግስት በመርከቧ ላይ ከባድ የሚባል ጉዳት እንደደረሰባት መግለጹ ይታወሳል።
በቀይ ባህር የሚደረጉ የመርከብ እንቅስቃሴዎች ደህንነት ለማስጠበቅ፣ አሜሪካ እና ዩኬ በየመን ግዛት ውስጥ በሀውቲ ይዞታዎች ላይ ተደጋጋሚ ድብደባ አካሂደዋል።
ይሁን እንጅ የሀውቲ ታጣቂዎችም በመርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት አላቆሙም።