ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የረሃብ አደጋ ለተጋረጠባቸው ህጻናት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መበጀቱን ገለጸ
በአፍሪካ 44 ሚሊዮን ህጻናት የረሃብ አደጋ አለባቸው ተብሏል
ኢትዮጵያን ጨምሮ በ27 የአፍሪካ ሀገራት በርካታ ህጻናት የረሃብ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተገልጿል
ወርልድ ቪዥን በአፍሪካ የረሃብ አደጋ ለተጋረጠባቸው ህጻናት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መበጀቱን ገለጸ፡፡
ዓለም አቀፉ የረድኤት ድርጅት ወርልድ ቪዥን በአፍሪካ የረሃብ አደጋ ያንዣበባቸው ህጻናትን ለመታደግ አዲስ የቀረጸውን ፕሮራም ይፋ አድርጓል፡፡
ድርጅቱ ለዚህ ፕሮግራሙ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በጀት መመደቡን የገለጸ ሲሆን ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ27 የአፍሪካ ሀገራት እንደሚተገበር ተገልጿል፡፡
እንደ ድርጅቱ ሪፖርት ከሆነ በአፍሪካ 342 ሚሊዮን ህዝብ ብርቱ የምግብ ዋስትና ችግር ሲኖርባቸው ይህ አሃዝ በዓለም ላይ ካሉ አጠቃላይ የምግብ ዋስትና ችግር ካለባቸው ህዝቦች መካከል የአንድ ሶስተኛ ድርሻ አለው፡፡
እንዲሁም በአፍሪካ 278 ሚሊዮን ህዝብ ያህሉ በቂ ምግብ የሌለው ሲሆን ከዚህ ውስጥ 55 ሚሊዮን ያህሉ ከአምስት ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ህጻናት እንደሆኑም የድርጅቱ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በዚህ ሪፖርት ምክንያት ወርልድ ቪዥን የ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን በቀጣዮቹ ሶት ዓመት እንደሚተገበሩ ተገልጿል፡፡
ይህ የሶስት ዓመት ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ27 የአፍሪካ ሀገራት ያሉ የረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ ችግር የተጋረጠባቸውን ህጻናት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
በአፍሪካ ከህጻናት በተጨማሪ በከተማ የሚኖሩ ዜጎች የምግብ ዋስትናቸው አደጋ ላይ የወደቁ 68 ሚሊዮን ዜጎች እንዳሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል፡፡
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል፡፡
እንደ ተቋሙ ሪፖርት ከሆነ ከአጠቃላይ ተፈናቀዮች ውስጥ 64 በመቶ ያህሉ በጦርነት እና ግጭት ምክንያት ሲፈናቀሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድርቅ እና ማህበራዊ ጭንቀት ምክንያት ነው፡፡
አይኦኤም ባሳለፍነው ነሀሴ እና መስከረም ወር ላይ አደረኩት ባለው ጥናት በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው እየተፈናቀሉ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት ትክክለኛ የተፈናቃዮችን ቁጥር ማግኘት እንዳልቻለ የገለጸው አይኦኤም ሶማሊ ክልል በድርቅ ከተፈናቀሉ ተፈናቃዮች መካከል ትልቁን ቁጥር እያስተናገደ ነውም ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መንግስታዊው የአደጋ መከላከል እና መቆጣጠር ኮሚሽን ከአንድ ወር በፊት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ከአጋር የረድኤት ድርጅቶች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ በግጭት እና ድርቅ ምክንያት ለተፈናቀሉ እና ሌሎች ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አድርጌያለሁ ማለቱ አይዘነጋም፡፡