የፑቲን ዋነኛ ተቀናቃኝ የነበረው ናቫልኒይ አስከሬን ለእናቱ ተሰጠ
የናቫልኒይ ቃል አቀባይ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንደጻፉት "ቤተሰብ የሚፈልገው እና አሌክሲ የሚገባው ይሆናል" ብለዋል
የናቫልኒይ እናት ባለፈው አርብ እለት የሩሲያ መርማሪዎች አስከሬኑን ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ገለጸው ነበር
የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ዋነኛ ተቀናቃኝ የነበረው አሌክሲ ናቫልኒይ አስከሬን ለእናቱ ተላልፎ ተሰጥቷል።
ባለፈው ሳምንት ባልተጠበቀ ሁኔታ ከሞስኮ በ1900 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የአርክቲክ እስርቤት ህይወቱ ያለፈው የሩሲያው ተቀዋሚ ናቫልኒይ አስከሬን ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ለእናቱ ተላልፎ መሰጠቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
የናቫልኒይ ቃል አቀባይ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንደጻፉት "ቤተሰብ የሚፈልገው እና አሌክሲ የሚገባው ይሆናል" ብለዋል።
የናቫልኒይ ባለቤት ዩሊያ ናቫልናያ ከአንድ ቀን በፊት በዩቲዩብ ቻናሏ ላይ ባስተላለፈችው መልእክት አስከሬኑ እንዲለቀቅ ጠይቃለች፤ በባሌቤቷ ላይ ተፈጽሟል ላለችው የማሰቃየት ተግባርም ፕሬዝደንት ፑቲንን ከሳለች።
የናቫልኒይ እናት ባለፈው አርብ እለት የሩሲያ መርማሪዎች አስከሬኑን ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ገለጸው ነበር።
ባለስልጣናት አስከሬኑን ለእናቱ የሰጡት፣ እናቱ ህዝብ ሳይሰበሰብ ለመቅበር በመስማማታቸው ምክንያት ነው ተብሏል።
የሩሲያ ባለስልጣናት እናቱ መንግስት ባቀረበው ቅደመ ሁኔታ የማይስማማ ከሆነ አስከሬኑን በእዚያው በእስር ቤት እንቀብረዋለን ሲሉ ማስፈራራታቸው ተገልጿል።