ባለፉት 4 ዓመታት ውስጥ 400 ሺህ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያን ከሳውዲ አረቢያ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል
ባለፉት 13 ቀናት ውስጥ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል
አይ.ኦ.ኤም እነዚህ ከስደት ተመላሽ ዜጎቸን ለመርዳት 742 ሺህ ዶላር ወጪ ማድረጉን ገልጿል
ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ 400 ሺህ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያን ከሳውዲ አረቢያ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) ገለጸ።
አይ.ኦ.ኤም ባለፉት አራት አመታት ውስጥ በሳውዲ አረቢያ ህጋዊ የጉዞ ሰነድ እና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው ቀርቶ ህይወታቸውን በእስር ቤት ይመሩ የነበሩ 400 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን አስታውቋል።
ድርጅቱ ለአል ዐይን አማርኛ በላከው መግለጫ እንደጠቆመው በህገወጥ ደላሎች እና በተሳሳቱ መረጃዎች ተታለው ወደ ሳውዲ አረቢያ የገቡ ዜጎች በተደጋጋሚ ለችግር እየተጋለጡ ነው።
በመሆኑም ከሳውዲአረቢያ እና ከኢትዮጵያ መንግስት በተጨማሪ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ጋር በመነጋገር ስደተኞቹን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
እነዚህን ስደተኞች የስነ ልቦና፣ የጤና፣ የትራንስፖርት እና ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎች ተሰጥቷቸዋል ያለው አይ.ኦ.ኤም 742 ሺህ ዶላር ወጪ ማድረጉን ገልጿል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ባለፈው ዓመት በችግር ላይ የነበሩ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያንን መመለስ እንዳልተቻለ የተገለጸ ሲሆን አሁን ላይ በስፋት ዜጎችን ወደ አገራቸው የማምጣቱ ስራ መቀጠሉንም ድርጅቱ በመግለጫው ጠቁሟል።
ባለፉት 13 ቀናት ውስጥ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ በሳውዲ አረቢያ በችግር ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን ከ23 ሺህ በላይ የሚሆኑት ስደተኞች እድሜያቸው ከ18 እስከ 29 ዓመት እንዲሁም 3 ሺህ ያህሉ ደግሞ ከ17 ዓመት በታች ናቸው።
ከነዚህ የሳውዲ አረቢያ ተመላሽ ኢትዮጵያዊያን መካከል ከአማራ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች በቅደም ተከተል ብዙ ነዋሪዎቻቸው የተሰደዱባቸው እና አሁን የተመለሱባቸው ክልልች ናቸው።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከሁለት ወር በፊት ባወጣው መግለጫ ተፈናቃይ እና ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት 111 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ማለቱ ይታወሳል።
ድርጅቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ እና ከጎረቤት እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት የተመለሱ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት 111 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ገልጾ ነበር።
በኢትይጵያ ከ27 በላይ የዓለማችን አገራት 800 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞችም ተጠልለው ህይወታቸውን በመምራት ላይ ሲሆኑ ፣ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ ከኡጋንዳ በመቀጠል ሁለተኛዋ አገር መሆኗንም ድርጅቱ ገልጿል።