መንገደኞችን የናጠው የሲንጋፖር አየርመንገድ አውሮፕላን ያለመዳረሻው ለማረፍ ተገዷል
211 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው አውሮፕላን በገጠመው ችግር አንድ መንገደኛ ህይወቱ ማለፉና 30 ሰዎች መቁሰላቸው ተገልጿል
ከአለማችን ቀዳሚ አየርመንገዶች መካከል ተጠቃሽ የሆነው የሲንጋፖር አየርመንገድ በቅርብ አመታት ውስጥ መሰል ችግር አልገጠመውም ተብሏል
ከለንደን የተነሳውና መዳረሻውን ሲንጋፖር ያደረገው ቦይንግ 777 አውሮፕላን በባንኮክ በድንገት ለማረፍ ተገዷል።
የሲንጋፖር አየርመንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን 211 መንገደኞችና 18 የበረራ ቡድን አባላትን አሳፍሮ ነበር ተብሏል።
ከለንደን ከተነሳ ከ11 ስአት በኋላ ሲበርበት ከነበረው 37 ሺህ ጫማ ከፍታ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ወደ 31 ሺህ ጫማ መውረዱን ፍላይትራዳርን ጠቅሶ ሬውተርስ ዘግቧል።
የአውሮፕላኑ ከሚበርበት ከፍታ በፍጥነት ዝቅ ማለት የመቀመጫቸውን ቀበቶ ያላሰሩ መንገደኞች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል።
“አውሮፕላኑ በፍጥነት ዥው ብሎ መውረድ ቀበቶ ያላሰሩ መንገደኞችን ከእቃ መጫኛው ጋር አጋጭቶ ወደ ወለሉ እንዲወረወሩ አድርጓል” ብሏል ዛፍራን አዝሚር የተባለ መንገደኛ።
የታይላንድ መገናኛ ብዙሃን በዚህ የአየር ጉዞ መረበሽ የአንድ መንገደኛ ህይወት ማለፉንና 30 ሰዎች መቁሰላቸውን ዘግበዋል።
የሲንጋፖር አየርመንገድ ደረሰ ስለተባለው የመንገደኞች ጉዳትና የአደጋው መንስኤ እስካሁን ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም።
አውሮፕላኑ በድንገት ያረፈበት የባንኮክ ሱቫርናሁሚ አውሮፕላን ማረፊያ ግን የአንድ መንገደኛ ህይወት ማለፉን አረጋግጧል።
በአየር ጸባይ እና ሌሎች ምክንያቶች በበረራ ወቅት ከአውሮፕላኖች መንገራገጭ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አደጋዎች በአየር ትራንስፖርት ላይ ደጋግመው ይታያሉ።
ከፈረንጆቹ 2009 እስከ 2018 ድረስ ባሉ አመታት ውስጥ ከተመዘገቡ የአውሮፕላን አደጋዎች ውስጥ ሲሶው በአውሮፕላኖች የጉዞ መረበሽ ወይም መናጥ ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው ይላል የአሜሪካ ብሄራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ።
ክስተቶቹ መንገደኞችን ለጉዳት ቢዳርጉም በአውሮፕላኖች ላይ ምንም ችግር እንዳልፈጠሩም በማከል።
በመሆኑም መንገደኞች በበረራ ወቅት የመቀመጫቸውን ቀበቶ እንዲያስሩ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎች የሚተላለፉት ለዚህ መሆኑንም አውስቷል።
ከአለማችን ቀዳሚ አየርመንገዶች መካከል ተጠቃሽ የሆነው የሲንጋፖር አየርመንገድ በቅርብ አመታት ውስጥ መሰል ችግር አልገጠመውም ተብሏል።
አየርመንገዱ ከሲንጋፖር ወደ ሎስ አንጀለስ ሲበር የነበረ አውሮፕላኑ በታይዋን ታይፒ ለማረፍ ሲሞክር ተከስክሶ የ83 መንገደኞች ህይወት ከተቀጠፈበት የጥቅምት 2000 አደጋ ወዲህ ከባድ አደጋ እንዳልገጠመው ሬውተርስ በዘገባው አመላክቷል።