የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በቱርክ እና ሴኔጋል አደጋ አጋጠማቸው
በሴኔጋል መዲና ዳካር በማረፍ ላይ እያለ ባጋጠመው የቴክኒክ አደጋ 11 ሰዎች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል
በቱርክ ደግሞ በማረፍ ላይ እያለ ጎማው እንደወለቀ ሲገለጽ በተሳፋሪዎች ላይ ጉዳት አላደረሰም
ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በቱርክ እና ሴኔጋል አደጋ አጋጥሞታል፡፡
የዓለማችን ቁጥር አንድ የአቪዬሽን ተቋም የሆነው ቦይንግ ኩባንያ 737 ማክስ የተሰኘው ምርቱ ከጥራት ጋር በተያያዘ ያጋጠመው ችግር ፈተና እንደሆነበት ቀጥሏል፡፡
አዲሱ የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ከገባ በኋላ በ737 ማክስ አውሮፕላን ምርቱ ላይ የበር መገንጠል፣ መስኮት መገንጠል፣ በበረራ ወቅት የጎማ መውደቅ እና ሌሎችም ችግሮች አጋጥሞታል፡፡
አሁን ደግሞ በቱርክ እና ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴኔጋል ተመሳሳይ የቴክኒክ ብልሽቶችን አስተናግዷል የተባለ ሲሆን በተወሰኑ መንገደኞች ለይ ቀላል ጉዳት ከማስተከተሉ በቀር የከፋ ችግር እንዳላጋጠመ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ንብረትነቱ የሴኔጋል አየር መንገድ የሆነ የበረራ ቁጥሩ ቢ737/300 የተሰኘ ማክስ አውሮፕላን 78 ወደ ማሊ መዲና ባማኮ መንገደኞችን አሳፍሮ እየተጓዘ የነበረ አውሮፕላን ተገዶ ዳካር ኤርፖርት ለማረፍ ተገዷል ተብሏል፡፡
አውሮፕላኑ ለማረፍ በተገደደበት ወቅትም በ11 መንገደኞች ላይ ጉዳት ሲደርስ በአራቱ ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት እንደደረሰ እና የአደጋው ምክንያት እየተመረመረ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
አፍሪካ እና አውሮፓ በባቡር ትራንስፖርት ሊገናኙ ነው ተባለ
ከዚሁ 737 ማክስ አውሮፕላን ጋር በተያያዘ በቱርክ 190 መንገደኞችን አሳፍሮ የነበረ አውሮፕላን ለማረፍ ሲሞክር ጎማዎቹ ተገንጥለው አደጋ አጋጥሟል ተብሏል፡፡
በቱርክ መቀመጫውን ያደረገው እና ኮሬንደን ኩባንያ ንብረት የሆነው አውሮፕላኑ ጎማዎቹ በመገንጠላቸው ምክንያት በአፍንጫው ለመቆም ተገዷል የተባለ ሲሆን በተሳፋሪዎቹ ላይ አደጋ እንዳላጋጠመ ተገልጿል፡፡
አውሮፕላኑ ከጀርመኗ ኮሎኝ ከተማ የተነሳ ነበር የተባለ ሲሆን ባጋጠመው አደጋ ምክንያት አንታሊያ ኤርፖርት እንዲያርፍ፣ ተሳፋሪዎችንም ከጉዳት ማዳን ተችሏል ሲል የቱርክ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡