የአርቲስት ሃጫሉን መገደል ተከትሎ በተከሰተው ሁከት ግድያ የፈጸሙ ሰዎች እስከ 22 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ
ከአጠቃላጥ ተከሳሾችውስጥ 90 በመቶ በሚሆኑት ላይ የቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈባቸውም ተገልጿል
በ6 ዞኖች በ3,373 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተለያዩ አካባቢዎች የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በተከሰተው ሁከት እና ብጥብጥ ዉስጥ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በፈጸሙ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ በማድረግ በ6 ዞኖች በ3,373 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ በመመስረት በህግ እንዲጠየቁ የማድረጉ ስራ መሰራቱን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡
በዚህም መሰረት ከላይ ከተጠቀሰው የተከሳሾች ቁጥር ውስጥ 90 በመቶ በሚሆኑት ላይ የቅጣት ውሳኔ እንዲተላለፍባቸው ማድረግ የተቻለ ሲሆን ከተሰበሰቡት ማስረጃዎችም መካከል ከ90 በመቶ የማያንሱ ምስክሮች በችሎት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸው ተገልጿል፡፡
በቅርብ ቀን ሰፊ መግለጫ እንደሚሰጥ ያስታወቀው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፣ ከወንጀል ድርጊቶቹ መካከል አንዱን በተመለከተ ፍርድ ቤት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
በተከሳሾች እነ ጂሎ በዳሶ (35 ሰዎች) መዝገብ ከቀረቡት 11 ተከሳሾች መካከል፡-
2ኛ ተከሳሽ (ሀቢብ በሪሶ)፣ 5ኛ ተከሳሽ ( አማን አቤ)፣ 6ኛ ተከሳሽ (ሙስጠፋ ዋሪሶ) እና 8ኛ (ሮባ ኤዳኦ) የተባሉ ተከሳሾች በወንጀል ህግ አንቀጽ 240/3፣ 539(1ሀ) እና 690(1ለ) መሰረት በኦሮሚያ ብ/ክ/መ ምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ 01 ቀበሌ በቡድን በመሆን በቀን 23/10/2013 ዓ.ም. ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ሲሆን የሟች አቶ ገለታው አውላቸው መኖሪያ ቤት ቅጥር ጊቢ ሰብሮ በመግባት በአምስት (05) የቤተሰብ አባላት ላይ የግድያ ወንጀል በመፈጸም እና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል ተሳትፈዋል በሚል ፤እንዲሁም 7ኛ ተከሳሽ (ሮባ አማን)፤ 14ኛ ተከሳሽ (ከድር ራበቶ)፣ 16ኛ ተከሳሽ (አለሙ ነጋሽ) እና 17ኛ ተከሳሽ (ሚኪ ጉዬ) በወንጀል ህግ አንቀጽ 240/3 እና 690(1ለ) ስር ተከሰው ክርክር ሲደረግ ከቆየ በኋላ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀን 17/07/2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የጥፋተኝነት ዉሳኔ በመስጠት የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከተቀበለ በኋላ እንደ ወንጀል ተሳትፎአቸው፡-
2ኛ ተከሳሽ (ሀቢብ በሪሶ) በ 20/ሀያ/ ዓመት ጽኑ እስራት
5ኛ ተከሳሽ (አማን አቤ) በ 22/ሀያ ሁለት/ ዓመት ጽኑ እስራት
6ኛ ተከሳሽ (ሙስጠፋ ዋሪሶ) በ 20/ሀያ/ ዓመት ጽኑ እስራት
8ኛ ተከሳሽ (ሮባ ኤዳኦ) በ 18 /አስራ ስምንት/ ዓመት ጽኑ እስራት
7ኛ ተከሳሽ (ሮባ አማን) እና 14ኛ ተከሳሽ (ከድር ራበቶ) በወንጀል ህግ አንቀጽ 488/1 እና 690/1ለ ስር እያንዳንዳቸዉ በ 1 (አንድ) ዓመት ከ ስምንት ወር ጽኑ እስራት እና 1000 ብር የገንዘብ መቀጮ፣
16ኛ ተከሳሽ (አለሙ ነጋሽ) እና 17ኛ ተከሳሽ (ሚኪ ጉዬ) በወ/ህግ አንቀጽ 488/1 / እና 690/1ለ/ ስር እያንዳንዳቸዉ በ 2 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በሙሉ ድምጽ ዉሳኔ ሰጥቷል፡፡
በዚህ እና በሌሎች መዛግብት ላይ በምስክርነት በመሳተፍ ለፍትህ ስርዓቱ ጉልህ ሚናችሁን ያበረከቱ ላላቸው አካላት ሁሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡