የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ
ድምጻዊው ከትናንት በስቲያ ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል
የ44 ዓመቱ ድምጻዊ ማዲንጎ ሶስት አልበሞችን ለአድማጮች አድርሷል
የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ስርዓተ ቀብር በዛሬው እለት ተፈጸመ።
ድምጻዊ ማዲንጎ ከሶስት ቀናት በፊት ማለትም መስከረም 17 ቀን 2015 ዓ.ም መጠነኛ ህመም ተሰምቶት በአዲስ አበባ ሰሚት አካባቢ ወደሚገኝ የህክምና ተቋም ባመራበት ወቅት ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል።
የአንድ ሴት ልጅ አባት የሆነው ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ በ44 ዓመቱ ህይወቱ አልፏል።
የድምጻዊው ስርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹ፣ አድናቂዎቹ እና የስራ ባልደረቦቹ በተገኙበት በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያ ተፈጽሟል።
ድምፆዊ ማዲንጎ አፈወርቅ በሰራቸው ሶስት ዓልበሞች ዘመን የሚሻገር ስራ ባለቤት ነበር።
"ስያሜ አጣሁላት" "አይደረግም" እና "ስወድላት" በተሰኙት አልበሞቹ እና በበርካታ ነጠላ ዜማዎቹ የሚታወቀው ድምጻዊ ማዲንጎ በሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ አይረሴ ያደርገዋል።
በጎንደር አዘዞ ተወልዶ በደብረታቦር ከተማ ያደገው ድምጻዊ ማዲንጎ አራተኛ አልበሙን ለአድማጮች ለማድረስ በመስራት ላይ እንደነበርም ሰምተናል።
የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ቤተሰቦች ለሙዚቃ ተሰጥኦ ያላቸው ሲሆን ታናሽ ወንድሙ ያሬድ አፈወርቅ እና እህቱ ትዕግስት አፈወርቅ ተወዳጅ የሆኑ የሙዚቃ ስራዎችን ሰርተው በሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ተወዳጆች ሆነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ህልፈት ሀዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በማህበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍም፤ “አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ በማረፉ የተሰማኝ ኀዘን ከባድ ነው” ብለዋል።
የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ህልፈትን ተከትሎ በርካታ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ በተለያየ መንገድ ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው። ጽምጻዊ ማዲንጎ ግንባር ድረስ በመሔድ እና በማሰልጠኛ ምልምሎችን በማነቃቃት ድርሻ ነበረው ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሃዘኑን ገልጿል፡፡