1ሺህ ቀናትን ባስቆጠረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ቴክኖሎጂዎች ሚና
ዩክሬን በዚህ ጦርነት ሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን እና አዳዲስ ፈጠራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሞክራለች
800 የሚጠጉ የዩክሬን የጦር መሳርያ አምራች ኩባንያዎች የተመሰረቱትም ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ነው
አድ ሺህ ቀናቶችን ያስቆጠረው የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ሮቦቶች ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎቶች እና አዳዲስ ወታደራዊ ስትራቴጂዎች የተዋወቁበት መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ለማጥቃት እና ጥቃትን ለመከላከል የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን መጠቀማቸው ሲነገር ይህም የጦርነቶችን አካሄድ እና ዘመናዊ የውግያ ስትራቴጂዎች በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተተገበሩበት ነው ተብሏል፡፡
ዩሪ ሼልሙክ የተባለው የጦር መሳርያ ቴክኖሎጂዎች አምራች ኩባንያ ባለቤት ከአመት በፊት የሰው አልባ ድሮኖችን አቅጣጫ እና የኢላማ ወሰን የሚያበላሽ ቴክኖሎጂን በባለፈው አመት ሲያስተዋውቅ የገበያ ፍላጎቱ ዝቅተኛ እንደነበር ይናገራል፡፡
በዚህኛው አመት ግን ይህን የቴክኖሎጂ መሳርያ በወር 2500 እንደሚያመርት እና መሳሪያው ካለው ተፈላጊነት የተነሳ ገዢዎች ቴክኖሎጂውን በእጃቸው ለማስገባት 6 ሳምንታትን መጠበቅ እንደሚገደዱ ለሮይተርስ ተናግሯል፡፡
በሁለቱም ወገን ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ሰው አልባ ድሮኖች በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ በዋሉበት ጦርነት ሩስያ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ከማጥቃት በዘለለ ኢላማዎችን ለመለየት አዲስ ወታደራዊ ስትራቴጂዎችን ጥቅም ላይ አውላለች፡፡
ሞስኮ እና ኪቭ በዚህ አመት 1.5 ሚሊየን ድሮኖችን ወደ ማምረት ሂደት የተቃረቡ ሲሆን ድሮኖቹ በትንሽ መቶ ዶላሮች የሚሰሩ እና በርቀት ቁጥጥር የሚደረግባቸው የጠላት ኢላማዎችን ለመለየት እና ለማጥቃት በብዛት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
ዩክሬን በበኩሏ ከምዕራባውያን ከምታገኝው ሰፊ የጦር መሳርያ ድጋፍ ባለፈ አዳዲስ የጦር መሳርያ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ሰፊ ጥረቶችን አድርጋለች፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ አብዘሀኞቹ ወደ 800 የሚጠጉ የዩክሬን የጦር መሳርያ አምራች ኩባንያዎች የተመሰረቱት ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ነው፡፡
በሁለቱም ወገኖች በወታደሮቻቸው ላይ የሚታየውን መሰላቸት እና የሞት መጠን ለመቀነስ የሰውን ልጅ በማሽን ለመተካት ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡
ሮይተርስ ከ7 የተለያዩ አለም አቀፍ የጦር መሳርያ አምራች ኩባንያዎች እና ወታደራዊ መኮንኖች አገኘሁት ባለው መረጃ ሰው አልባ ውጊያ የመጪው ጊዜ የጦር ሜዳ ውሎ ዋነኛ ትኩረት ሊሆን እንደሚችል ዘግቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት 160 የሚጠጉ የዩክሬን ኩባንያዎች ሰው አልባ ተሸከርካሪዎችን እያመረቱ ይገኛሉ። እነዚህ ተሸርካሪዎች የቆሰሉ ሰዎችን ለማስወጣት፣ ጦር መሳርያን ጨምሮ የተለያዩ ወታደራዊ ሎጂስቲኮችን ለማድረስ እንዲሁም በሚገጠምላቸው መትረየስ ጥቃት ለመፈጸም የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
ከዚህ ባለፈም በርቀት መቆጣጠርያ የሚሰሩ በሰው አልባ አነስተኛ ተሸከርካሪዎች ላይ የሚገጠሙ አውቶማቲክ ጦር መሳርያዎች ምርት ከሙከራ ደረጃ ተሻግረው ሰፊ ጥቅም እየሰጡ ነው ተብሏል፡፡
ምንም እንኳን ዩክሬን ተተኳሾን ፣ የሚሳኤል እና የአየር መከላከያ መሳርያዎች ላይ አሁንም በምዕራባውያን ሀገራት ድጋፍ ላይ ጥገኛ ብትሆንም፤ ከሶቪየት ዘመናት ጀምሮ ቆሞ የነበረውን የመከላከያ ማምረቻን ለማሻሻል 1.5 ቢሊዮን ዶላር አፍስሳለች ።
የዩክሬን 67ኛው ሜካናይዝድ ብርጌድ አዛዥ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት በምሽግ ውስጥ የሚሰማሩ እግረኛ ወታደሮች ቁጥር ቀንሷል፤ ከዚህ ይልቅ የውጊያ ትእዛዞች እና የኢላማ ጥቃቶች ከሩቅ ቦታ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወደ ማስፈጸም እየተቀየረ ነው ፡፡ ይህም የወታደሮችን ሞት ለመቀነስ አግዟል ባይ ናቸው፡፡
በፍጥነት እየተሻሻሉ ከሚገኙ የጦር ሜዳ ሁኔታዎች ጋር ተሰናስሎ ለመዝለቅ በሚደረገው ጥረት በሰማይ ፣ በመሬት እና በባህር ላይ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ መሳርያዎች እንዲሁም ፀረ-ድሮን ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ለማድረግ ያለው ፍላጎት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ታግዞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡