የህንዷ ዋና ከተማ ዴልሂ በከፍተኛ ጭጋግ ተሸፈነች
በዴልሂ እና ከዋና ከተማ በሰሜን ምዕራብ በኩል በምትገኘው ቻንዲጋር ከተሞች ማየት የሚቻልበት ርቀት ወደ 100 ሜትር ዝቅ ብሏል
የህንድ የብክለት ቁጥጥር ባለስልጣን እንደገለጸው የዋና ከተማዋ የአየር ጥራት ጠቋሚ 484 የደረሰ ሲሆን ይህም በዚህ አመት እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነው
የህንዷ ዋና ከተማ ዴልሂ በከፍተኛ ጭጋግ ተሸፈነች።
መርዛማ ጭጋግ አብዛኛውን የሰሜን ህንድ ግዛት የሸፈነ ሲሆን በዋና ከተማ ኒው ዴልሂ ያለው የአየር ጥራት ደግሞ በከፍተኛ መጠን ዝቅ ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ጭስ እና ጉም የቀላቀለው ጭጋግ ብዙ የሚከሰተው በክረምት ወቅት ነው። በክረምት ወቅት የሚኖረው ቀዝቃዛ አየር አቧራ፣ የተበከለ ጋዝ እና በከተማዋ አቅራቢያ ካሉ ህገወጥ እርሻዎች የሚወጣውን ጭስ ይስባል።
በዴልሂ እና ከዋና ከተማ በሰሜን ምዕራብ በኩል በምትገኘው ቻንዲጋር ከተሞች ማየት የሚቻልበት ርቀት ወደ 100 ሜትር ዝቅ ያለ ቢሆንም ባለስልጣናት የአየር እና የባቡር እንቅስቃሴ አለመስተጓጎሉን ገልጸዋል።
የህንድ የብክለት ቁጥጥር ባለስልጣን እንደገለጸው የዋና ከተማዋ የአየር ጥራት ጠቋሚ 484 የደረሰ ሲሆን ይህም በዚህ አመት እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነው።
የአየር ጥራት ደረጃ የሚሰጠው የስዊሱ አይኪውአየር መረጃ እንደሚያመለክተው የኒው ደልሂ የአየር ጥራት ደረጃው "አደገኛ" 1081 ሲሆን በአለም በከፍተኛ መጠን የተበከለች ከተማ ነች።
የዴልሂ ባለስልጣናት ዝቅተኛ የንፋስ ፍጥነት እና ተስማሚ ያልሆኑ ሁኔታዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የኦላይን ትምህርት እንዲሰጡ፣ የግንባታ ስራዎች እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች እንዲገደቡ አድርገዋል።
የሩዝ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ማሳውን ነጻ ለማድረግ የሚለኮሰው እሳት ለዴልሂ ብክለት 40 በመቶ አስተዋጽኦ ማድረጉን በመሬት ሳይንስ ሚኒስቴር ስር ያለው አየር ትንበያ ኤጀንሲ (ሳፋር) ገልጿል። የሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳዩት ከሆነ 1334 ማሳን በማቃጠል መሬትን ነጻ የማድረግ ተግባራት ተከናውነዋል።
አየሩ በከፍተኛ ሁኔታ የተበከለ ቢሆንም የከተማ ነዋሪዎች የተለመደ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ነው። የከተማዋ መገለጫ የሆነውን 'ኢንዲያ ጌት'ን ጨምሮ በርካታ ህንጻዎች አይታዩም።