ትዕግስት ገዛኸኝ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የፓራሊምፒክ ወርቅ አስገኘች
ማክሰኞ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም የተጀመረው የቶኪዮ ፓራሊምፒክ ውድድር ለ13 ቀናት የሚካሄድ ይሆናል
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ አትሌት ትዕግስት ለሰራችው ታሪክ እንኳን ደስ ያለሽ “ኢትዮጵያ ኮርታብሻለች!” ብለዋል
በጃፓን፣ ቶኪዮ እየተካሄደ ባለው የፓራሊምፒክ ውድድር ላይ በ1 ሺ500 ሜትር የሩጫ ውድድር ላይ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ ተመዝግቧል።
በኢትዮጵያ የፓራሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ በማግኘት ታሪክ ያስመዘገበችው ደግሞ አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ናት።
በውድድሩ የአሜሪካዋ አትሌት በሁለተኛነት የቱኒዝያዋ አትሌት ደግሞ በሦስተኛነት አጠናቀዋል።
በዘንድሮው ፓራሊምፒክ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ሦስት አትሌቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራሊምፒክ የተሳተፈችው እስራኤል፣ ቴል አቪቭ ውስጥ እ.አ.አ በ1968 በተካሄደው ውድድር ላይ እንደነበር ይታወሳል።
በ2012 በተካሄደው ፓራሊምፒክ ላይ አትሌት ወንድዬ ፍቅሬ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የብር ሜዳልያ አስመዝግቦ ነበር።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የብር ሜዳልያ ያገኘችው በ2016 በሪዮ ዲ ጄኔሮ የወንዶች 1500 ሜትር ሩጫ በአትሌት ታምሩ ደምሴ አማካይነት ነው።
የቶኪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ ኢትዮጵያ በፓራሊምፒክ ውድድር እስካሁን ስምንት አትሌቶችን አሳትፋለች።
ዛሬ ትዕግስት ገዛኸኝ ያስመዘገበችው የወርቅ ሜዳልያ በፓራሊምፒክ ታሪክ ለኢትዮጵያ ትልቁና ቀዳሚው ነው።
ማክሰኞ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም የተጀመረው የቶኪዮ ፓራሊምፒክ ውድድር ለ13 ቀናት ይካሄዳል።
ኢትዮጵያን በፓራሊምፒክ ውድድር የሚወክሉት አትሌት ታምሩ ከፍያለው፣ አትሌት ገመቹ አመኑ እና አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ናቸው።