የኮሮና ቫይረስ እስካሁን 81 ሰዎችን ለሞት ዳርጓል፡፡
እስካሁን ቫይረሱ በተከሰተበት ሁቤይ ግዛት ብቻ 77 ሰዎች ሲሞቱ፣ 4 ሰዎች ደግሞ በሌላ የቻይና አካባቢዎች በቫይረሱ ሞተዋል፡፡
በቻይና የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 2,761 ሲደርስ፣ ከቻይና ውጭ ደግሞ ከ50 በላይ ሰዎች ተይዘዋል፡፡
51 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመው ከሆስፒታል ወጥተዋል ነው የተባለው፡፡
የሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጋብሬል ሌዉንግ እንዳሉት ምልከት ያልታየባቸውን ታማሚዎች ጨምሮ የዉሀን ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር 44,000 ሊደርስ ይችላል፡፡ ቫይረሱ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ፣ ፕሮፌሰሩ ይሄን መላምታቸውን በማስረጃ አስደግፈው ለሀገሪቱ ባለስልጣናትና ለዓለም ጤና ድርጅት ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
የብሪታኒያ ሳይንቲስቶች ደግሞ እያንዳንዱ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ከሁለት እስከ ሶስት ሰዎችን እንደሚበክል ይፋ አድርገዋል፡፡
በአፍሪካ ኮት ዲቮር ላይ የመጀመሪያው ምልክት ትናንት መታየቱም እየተዘገበ ነው፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በሁቤይ ግዛት የቫይረሱ መነሻ ዉሃንን ጨምሮ ከ60 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላቸው 15 ከተሞች ተዘግተዋል፡፡
የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬቂያንግ የቫይረሱ ዋነኛ ተጠቂ በሆነችው በማዕከላዊ ቻይና ሁቤይ ግዛት በምትገኘው ዉሀን ከተማ ዛሬ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከተማዎ የሚገኙ ህመምተኞችን እና የህክምና ቡድን አባላትንም የጎበኙ ሲሆን እርሳቸውም እንደ አለቃቸው ሺ ጂንፒንግ ሁሉ መላው የሀገሪቱ ባለስልጣናት ሙሉ ትኩረታቸውን ቫይረሱን በመቆጣጠር ላይ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
ቻይና ቫይረሱን ለመቆጣጠር 12.8 ቢሊዮን ዶላር በጀት መመደቧም ተገልጿል፡፡
በዉሀን ለቫይረሱ ተጠቂዎች የሚገነባው ባለ 1,000 አልጋ የአስቸኳይ ጊዜ ሆስፒታል ግንባታም ሌት ተቀን በመከናወን ላይ ነው፡፡ ሆስፒታሉ በ 1 ሳምንት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡
ከቻይና ውጭ ታይላንድ(8) ፣ አውስትራሊያ (5)፣ ማሌዢያ(4)፣ ሲንጋፖር (4)፣ ፈረንሳይ (3)፣ ደቡብ ኮሪያ (3)፣ ጃፓን(3) ፣ዩኤስኤ (5)፣ታይዋን(4)፣ ቬትናም(2)፣ ኔፓል(1)፣ ካናዳ (1) እና ኮት ዲቮር (1) ምልክት የታየባቸው ሀገራት ናቸው፡፡
አሜሪካ ነገ ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም ዜጎቿን ከዉሀን ከተማ ለማስወጣት 240 መቀመጫዎች ያሉት ቦይንግ 767 አውሮፕላን ልትልክ ተዘጋጅታለች፡፡
ፈረንሳይ፣ አውስትራሊያና ህንድን ጨምሮ ሌሎች ሀገራትም ዜጎቻቸውን ከቻይናዋ ከተማ ማውጣት የሚችሉበትን አማራጭ በማሰብ ላይ ናቸው፡፡
በቻይናና ሩሲያ መካከል የምትገኘው ሞንጎሊያ ምንም እንኳን እስካሁን የቫይረሱ ምልክት ባይገኝባትም ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ከዛሬ ጀምሮ ለ 5 ሳምንታት ትምህርት ቤቶችን ዘግታለች፡፡
ሲኤንኤን፣ ሲጂቲኤን እና ቢቢሲ የዘገባው ምንጮቻችን ናቸው፡፡