ለስድስት አመታት በአልሸባብ ቁጥጥር ስር የቆየችው አዳን ያባል ከተማ ፥ የቡድኑ ታጣቂዎች ማሰልጠኛ ማዕከል ነበረች ተብሏል
የሶማሊያ ጦር አልሸባብን ለስድስት አመታት በቁጥጥሩ ስር አድርጓት ከቆየችው የአዳን ያባል ከተማ አስለቀቀ።
በአፍሪካ ህብረት ጥምር ጦርና በአካባቢው ሚሊሻዎች የታገዘው የሶማሊያ ጦር ከተማዋን ከአልሸባብ ታጣቂዎች ነጻ ማድረጉን የአፍሪካ ህብረት ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
በዚህ ውጊያም 700 የሚጠጉ የቡድኑ ተዋጊዎች መገደላቸውን ነው የከተማዋ ከንቲባ ማሃሙድ ሃሰን ማሃሙድ የተናገሩት።
በማዕከላዊ ሶማሊያ የምትገኘው ከተማዋ ከሞቃዲሾ 240 ኪሎ ሜትር ላይ ትገኛለች።
በመካከለኛው ሸበሌ ክልል የምትገኘው አዳን ያባል ማዕካላዊ ሶማሊያን ከደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል የምታስተሳስር ስትራቴጂክ ከተማ ናት።
አልሸባብም ላለፉት ስድስት አመታት ዋነኛ የማሰልጠኛ እና ተልዕኮ መምሪያ አድርጓት መቆየቱን ሬውተርስ አውስቷል።
ቡድኑ የከተማዋን ነዋሪዎች እንደ ሰብአዊ ጋሻ እየተጠቀም መሰረት ልማቶችንም ሲያፈራርስ መቆየቱን ነው ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ ሞሃሙድ የተናገሩት።
“በመኖሪያ መንደሮች መዋጊያ ምሽጎችን ገንብቶ ንጹሃንን መከላከያ አድርጓል፥ በመንግስት ከሚወሰድ የአየር ጥቃትም ሲያመልጥ ቆይቷል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ባለፉት ወራት የተወሰደበትን እርምጃ መቋቋም እንደተሳነው አብራርተዋል።
በመሆኑም የአዳን ያባል ከተማ በመንግስት ሃይሎች መያዝ ለንጹሃን እፎይታ፤ ለቡድኑ ደግሞ ትልቅ ኪሳራ ነው ብለዋል የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ መሪው ሞሃመድ ኤልአሚን ሶይፍ ያነሱት።
አልሸባብ ግን ከተማዋ ስለመያዟም ሆነ ስለቀረበበት ንጹሃንን የመጠቀም ወቀሳ ምንም ምላሽ አልሰጠም።
ቡድኑ ከመንግስት ጦር በሚሰነዘርበት ጥቃት የሚደርስበትን ኪሳራ ለመቀነስ ተቆጣጥሯቸው ከቆዩ ከተሞች በፍጥነት የመውጣት ልምድ አለው።
የሶማሊያ ጦርም ያስለቀቃቸውን ከተሞች ይዞ መቆየት እየተሳነው አልሸባብ ዳግም ከተሞቹን በእጁ ሲያስገባ ታይቷል።
በቡድኑ ላይ ጦርነት ያወጁት ፕሬዚዳንት ሃሰን ሼክ ሞሃሙድ ግን ያለፉ ስህተቶችን እንደሚያርሙ ይጠበቃል።