የሶማሊያ መንግስት፤ ሶማሊያውያን አልሻባብን “ኻዋሪጅ” ብለው እንዲጠሩ ጠይቋል
የሶማሊያ የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር በሀገሪቱ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት አስላማዊ ታጣቂዎችን “አልሻባብ” በሚል ስም እንዳይጠሩ ገደብ ጥሏል፡፡
አልሻባብ በአረቢኛ “ወጣት” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፤ የቀጠናው ስጋት የሆነው ጂሃዳዊ ታጣቂ ቡድን እንደሚጠቀምበት ይታወቃል፡፡
የሀገሪቱ ህዝብ ታጣቂውን ቡድን አልሻባብ ብሎ እንዳይጠራ ያገደው ሚኒስቴሩ፤ ከአሁን በኋላ “ኻዋሪጅ” ብሎ እንዲጠራው ጠይቋል፡፡
“ኻዋሪጅ” የሚለው ቃል ማጣጣል (ንቀት) የተሞላበት ቃል ሲሆን ፤ ትርጉሙ ደግሞ ምንም ነውር የማያውቅ ዱሪየ እንደማለት ነው ተብሏል፡፡
አዲሱ መመሪያ የመጣው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ በቡድኑ ላይ “ጦርነት” ካወጁ በኋላ ነው።
የኃይማኖት አባቶች ከአልቃዒዳ ጋር ግንኙነት ካላቸው ታጣቂዎች ጋር እንዳይገናኙና ምንም አይነት ስምምነት እንዳይኖራቸውም መከልከሉም የሶማሊያ የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አመላክቷል፡፡
የሶማሊያ መንግስት፤ አልሻባብን “ኻዋሪጅ” በሚል ስም እንዲጠራ መመሪያ ማስተላለፉ ከታጣቂው ጋር እየተደረገ ያለውን ትግል አካል እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ይሁን እንጅ የሶማሊያ ምንግስት አልሻባብን ሌላ ስም ሲሰጠው ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡
እንደፈረንጆቹ በ2015 ታጣቂ ቡድኑን "ኡጉስ" የሚል ስያሜ ሰጥቶት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የቃሉ ትርጉምም "የሶማሊያ ህዝብን የሚጨፈጭፍ ቡድን " የሚል መልዕክት እንዳለውም በወቅቱ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
አልሻባብ በወቅቱ በሰጠው ምላሽ መንግስት ላወረደው መመሪያ ተገዥ በሚሆኑ አካለት እንዲሁም ቃሉን በሚጠቀሙ ጋዜጠኞች ላይ እርምጃ እንደሚወስድም ዝቶ ነበር፡፡