አልሸባብ የሶማሊያ ባለስልጣናት በሚያዘወትሩት ሆቴል ላይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት አደረሰ
በጥቃቱ የደረሰው ጉዳት ባይገለፅም የሀገሪቱ ፓሊስ ፈጣን እርምጃ መውሰዱ ተነግሯል
የሽብር ቡድኑ በ2022 የፈፀመው ጥቃት ካለፈው አመት በ30 በመቶ መጨመሩን የመንግስታቱ ድርጅት ገልጿል
አልሸብብ በሶማሊያ የፕሬዚዳንቱ ቤተመንግስት አቅራቢያ በሚገኝ ሆቴል ላይ ጥቃት አደረሰ።
ቪላ ሮስ በተሰኘውና የሶማሊያ ሚኒስትሮች እና ህግ አውጪዎች በሚያዘውትሩት ሆቴል ነው አልሸባብ ጥቃቱን ያደረሰው።
የሶማሊያ ፖሊስ እንዳስታወቀው የአልሸባብ አጥፎቶ ጠፊ ትናንት በሆቴሉ በር ላይ ቦምብ አፈንድቷል። በመቀጠልም የተኩስ እሩምታ ከፍቷል።
ፓሊስ በአልሸባብ ታጣቂዎች ላይ ፈጣን እርምጃ መውሰዱን የገለፀ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎችን ከሆቴሉ ማስወጣት ተችሏል ብሏል።
የሀገሪቱ የአየር ንብረት ሚኒስትር ድኤታው አደም ሂርሲ ከጥቃቱ ማምለጣቸውን በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
አልሸባብ ሀላፊነቱን በወሰደበት ጥቃት የደረሰው የጉዳት መጠን እስካሁን አልተገለፀም።
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በአልሸባብ ላይ ጦርነት በማወጃቸው የቡድኑ የአጥፎቶ መጥፋት ጥቃት እየጨመረ መጥቷል።
ባለፈው ወር ብቻ በጥቂቱ 120 ሰዎችን ህይወት የቀጠፉ ሁለት የቦምብ ጥቃቶች በአልሸባብ ተፈፅመዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት መረጃም በፈረንጆቹ 2022 ቡድኑ በሶማሊያ የ613 ሰዎችን ለገደሉና ከ940 በላዬቹን ላቆሰሉ ጥቃቶች እጁ አለበት።
የጥቃቱ መጠን በ2021 ከነበረው በ30 በመቶ አድጓል።
የደረሰው የጉዳት መጠንም ከ2017 ወዲህ ከፍተኛው ነው መባሉን ሬውተርስ አስነብቧል።
የሶማሊያ ጦር በደቡባዊ እና ማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል በአልሸባብ ላይ የተጠናከረ እርምጃ መውሰዱን ቀጥሏል።
የሀገሪቱ መንግስት አለም አቀፍ ድጋፍን በሚሻበት ወቅት የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሀገሪቱ ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ እቀባ ማራዘሙ ቅሬታን ፈጥሯል።