ፑቲን ያስቀመጡት ግብ ሳይሳካ የዩክሬኑ ጦርነት እንደማይቆም ክሬሚሊን አስታወቀ
ፑቲን ዩክሬን ወደ ኔቶ የመግባት ሀሳቧን እንድትተው እና ሩሲያ በከፊል ከያዘቻቸው አራት ግዛቶቿ ለቃ እንድትወጣ ይፈልጋሉ
ዘለንስኪ ጦርነቱ በድርድር እንዲያልቅ እና ኔቶን እስከምትቀላቀል ድረስ የውጭ ወታደሮች በዩክሬን እንዲሰማሩ ሀሳብ አቅርበዋል
ፑቲን ያስቀመጡት ግብ ሳይሳካ የዩክሬኑ ጦርነት እንደማይቆም ክሬሚሊን አስታወቀ።
የሩሲያ ቤተመንግስት ክሬሚሊን የዩክሬኑ ጦርነት በፕሬዝደንት ፑቲን የተቀመጡት ግቦች በወታደራዊ እርምጃ ወይም በድርድር እስከሚሳኩ ድረስ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ፑቲን ዩክሬን ወደ ኔቶ የመግባት ሀሳቧን እንድትተው እና ሩሲያ በከፊል ከያዘቻቸው አራት ግዛቶቿ ለቃ እንድትወጣ ይፈልጋሉ። ዩክሬን ግን ይህን ቅድመ ሁኔታ እጅ እንደመስጠት ስለምትቆጥረው ውድቅ አድርጋዋለች።
"ልዩ ወታደራዊ ዘመቻው የሚጠናቀቀው ፕሬዝደንት ፑቲን እና ኢታማዦር ሹሙ ያስቀመጧቸው አላማዎች ሲሳኩ ነው" ሲሉ የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል።
ፔስኮቭ እንደገለጹት እነዚህ ግቦች የሚሳኩት እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ ወይም አግባብነት ባለው ድርድር ነው።
ፔስኮቭ "በዩክሬን በኩል ለድርድር ፍቃደኝነት ባለመኖሩ"በአሁኑ ወቅት በሞስኮ እና ዩክሬን መካከል ንግግር የለም ብለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሰኞ እለት ጦርነቱ በድርድር እንዲያልቅ እና ኔቶን እስከምትቀላቀል ድረስ የውጭ ወታደሮች በዩክሬን እንዲሰማሩ ሀሳብ አቅርበዋል።
ሶስት አመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ብቻ የሚቀሩት የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት በቅርቡ ምዕራባውያን ዩክሬን የረጅም ርቀት ተጠቅማ ሩሲያን እንድታጠቃ መፍቃዳቸው እና ሩሲያ ይህን ተከትሎ ኦሬሽኒክ የተባለ አዲስ ሚሳይል መተኮሷ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ ተስተውሎ ነበር።