የሶማሊያ መንግስት እና ተመድ የርሀብ ተጋላጮችን ለመታደግ ከ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ጠይቀዋል
15 ሚሊዮን አካባቢ ከሚገመተው የሶማሊያ ህዝብ 4 ሚሊዮን ሰዎች በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ለርሀብ መጋለጣቸው ተገልጿል፡፡ በሽታ ፣ የበረሀ አምበጣ ወረርሽኝ ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ማባሪያ ያጣው ግጭት በዓመቱ ይከሰታል ለተባለው ከፍተኛ የምግብ እጥረት ምክንያት መሆናቸውን ነው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ አዳም አብደልሙላ የገለጹት፡፡
በዚህ ዓመት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋጥማቸዋል የተባሉ 4 ሚሊዮን ሶማሊያውያንን ለመታደግ ፣ የተባበሩት መንግስታት እና የሶማሊያ መንግስት ዛሬ ሰኞ የካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም የ 1.09 ቢሊዮን ዶላር የዕርዳታ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ሁለቱ አካላት በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ፣ ከፍተኛ የምግብ እጥረት የሚገጥማቸው ሶማሊያውያን ቁጥር በ2021 በአንድ ሚሊዮን ይበልጣል፡፡
ችግሩን ለመቋቋም የተጠየቀው ገንዘብ እንደ ምግብ ፣ መጠለያ እና የጤና አገልግሎቶች ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያገለግል የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣኑ ሚስተር አዳም አስታውቀዋል፡፡
የሶማሊያ የሰብዓዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ከዲጃ ዲሪዬ ፣ የሀገሪቱ የሰብዓዊ ችግሮች በህይወት አድን ድጋፎች ብቻ ሊቀረፉ እንደማይችሉ ገልጸው ፣ የልማት አጋሮች ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል ድጋፍ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ለርሀብ ይጋለጣሉ የተባሉትን ጨምሮ ባጠቃላይ 5.9 ሚሊዮን ሶማሊያውያን በዚህ ዓመት የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ነው የተባለው፡፡ የሀገሪቱ ሚዲያ የሆነው ጎብ ጆግ እንደዘገበው ባለፈው ዓመት ተረጂ የነበሩ የሀገሪቱ ዜጎች 5.2 ሚሊዮን ነበሩ፡፡